ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 16:2-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ሳሙኤል ግን፣ “ሳኦል ከሰማ ስለሚገድለኝ እንዴት መሄድ እችላለሁ?” አለ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “አንዲት ጊደር ይዘህ ሂድና፣ ‘ለእግዚአብሔር ልሠዋ መጥቻለሁ’ በል።

3. እሴይን ወደ መሥዋዕቱ ጥራው፤ ከዚያም የምታደርገውን አሳይሃለሁ፤ የምነግርህንም ሰው ትቀባልኛለህ።”

4. ሳሙኤል እግዚአብሔር ያለውን ነገር አደረገ። ቤተ ልሔም እንደ ደረሰም፣ የከተማዪቱ ሽማግሌዎች እየተንቀጠቀጡ ሊገናኙት መጡ፣ እነርሱም “አመጣጥህ ለሰላም ነውን?” ብለው ጠየቁት።

5. ሳሙኤልም፣ “አዎን፤ ለሰላም ነው፤ የመጣሁትም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ላቀርብ ነው፤ እናንተም ራሳችሁን ቀድሳችሁ ከእኔ ጋር ወደ መሥዋዕቱ ኑ” ሲል መለሰላቸው። ከዚያም እሴይንና ልጆቹን ቀደሳቸው፤ ወደ መሥዋዕቱም እንዲመጡ ጠራቸው።

6. እዚያ በደረሱ ጊዜም፣ ሳሙኤል ኤልያብን አይቶ፣ “በእርግጥ እግዚአብሔር የቀባው ሰው እነሆ፤ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞአል” ብሎ አሰበ።

7. እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፣ “መልኩን ወይም ቁመቱን አትይ፤ እኔ ንቄዋለሁና። እግዚአብሔር የሚያየው፣ ሰው እንደሚያየው አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” አለው።

8. ከዚያም እሴይ አሚናዳብን ጠርቶ በሳሙኤል ፊት እንዲያልፍ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን፣ “እግዚአብሔር ይህንንም አልመረጠውም” አለው።

9. እሴይም ሣማን አሳለፈ፤ ሳሙኤልም፣ “እርሱንም እግዚአብሔር አልመረጠውም” አለ።

10. እሴይም ሰባቱን ልጆቹን በሳሙኤል ፊት እንዲያልፉ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን፣ “እግዚአብሔር እነዚህንም አልመረጣቸውም” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 16