ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ገላትያ 3 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እምነት ወይስ የኦሪትን ሕግ መጠበቅ

1. እናንተ የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ! ለመሆኑ ማን መተት አደረገባችሁ? ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ በፊት ለፊታችሁ በግልጥ ተሥሎ ነበር።

2. ከእናንተ ዘንድ አንድ ነገር ብቻ ማወቅ እፈልጋለሁ፤ መንፈስን የተቀበላችሁት ሕግን በመጠበቅ ነው ወይስ የተሰበከላችሁን በማመን?

3. ይህን ያህል የማታስተውሉ ናችሁን? በመንፈስ ጀምራችሁ በሥጋ ፍጹም ለመሆን ትጥራላችሁን?

4. በርግጥ ለከንቱ ከሆነ፣ ይህን ያህል መከራ የተቀበላችሁት እንዲያው ነውን?

5. እግዚአብሔር መንፈሱን የሚሰጣችሁ፣ በእናንተም ዘንድ ታምራትን የሚሠራው ሕግን ስለ ጠበቃችሁ ነው ወይስ የሰማችሁትን ስላመናችሁ?

6. እስቲ አብርሃምን አስቡ፤ “እርሱ እግዚአብሔርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት።”

7. እንግዲህ እነዚያ የሚያምኑት የአብርሃም ልጆች እንደሆኑ አስተውሉ።

8. መጽሐፍ፣ እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቅ አስቀድሞ በማየት፣ “አሕዛብ ሁሉ በአንተ ይባረካሉ” በማለት ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ አስታወቀው።

9. ስለዚህ በእምነት የሆኑት፣ የእምነት ሰው ከሆነው ከአብርሃም ጋር ቡሩካን ናቸው።

10. ሕግን በመጠበቅ የሚተማመኑ ሁሉ ከርግማን በታች ናቸው፤ “በሕግ መጻሕፍት የተጻፈውን ሁሉ የማያደርግ የተረገመ ነው” ተብሎ ተጽፎአልና።

11. “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ስለ ተባለ፣ ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንደማይጸድቅ ግልጽ ነው።

12. ሕግ በእምነት ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ ነገር ግን “ሕግጋትን የሚፈጽም ሰው በእነርሱ በሕይወት ይኖራል” ተብሎአል።

13. “በዕንጨት ላይ የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ስለ ተጻፈ፣ ክርስቶስ ስለ እኛ ርግማን ሆኖ ከሕግ ርግማን ዋጅቶናል፤

14. ለአብርሃም የተሰጠው በረከት፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ለአሕዛብ እንዲደርስ ዋጅቶናል፤ ይኸውም በእምነት የመንፈስን ተስፋ እንድንቀበል ነው።

የኦሪት ሕግና የተስፋ ቃል

15. ወንድሞች ሆይ፤ ከሰው ዕለታዊ ሕይወት የተለመደውን ምሳሌ አድርጌ ላቅርብ፤ የሰው ኪዳን እንኳ አንድ ጊዜ ከጸደቀ በኋላ ማንም ሊሽረው ወይም በእርሱ ላይ ሊጨምርበት እንደማይችል ሁሉ፣ በዚህም ጒዳይ ቢሆን እንደዚሁ ነው።

16. የተስፋውም ቃል የተነገረው ለአብርሃምና ለዘሩ ነበር፤ መጽሐፍ፣ ለብዙ ሰዎች እንደሚነገር፣ “ለዘሮቹ” አይልም፤ ነገር ግን ለአንድ ሰው እንደሚነገር፣ “ለዘርህ” ይላል፤ እርሱም ክርስቶስ ነው።

17. የምለው እንዲህ ነው፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ፣ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የጸናውን ኪዳን አፍርሶ የተስፋውን ቃል አይሽርም።

18. ርስትን መውረስ በሕግ ቢሆን ኖሮ፣ በተስፋ ቃል ባልተገኘ ነበርና፤ እግዚአብሔር ግን በጸጋው በተስፋ ቃል አማካይነት ለአብርሃም ሰጥቶታል።

19. ታዲያ ሕግ የተሰጠበት ምክንያት ምንድን ነው? ሕግ የተጨመረው ከመተላለፍ የተነሣ ተስፋው ያመለከተው ዘር እስኪመጣ ድረስ ነበር፤ ሕጉም የመጣው በመላእክት በኩል፣ በአንድ መካከለኛ እጅ ነበር።

20. ሆኖም መካከለኛው አንድን ወገን ብቻ የሚወክል አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።

21. ታዲያ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የሚቃወም ነውን? ከቶ አይደለም፤ ሕግ የተሰጠው ሕይወትን ለማስገኘት ቢሆን ኖሮ፣ በርግጥም ጽድቅ በሕግ በኩል በተገኘ ነበር።

22. መጽሐፍ ግን ዓለም ሁሉ የኀጢአት እስረኛ መሆኑን ያውጃል፤ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው ተስፋ ለሚያምኑት ሁሉ ይሰጥ ዘንድ ነው።

23. ይህ እምነት ከመምጣቱ በፊት በሕግ አማካይነት እስረኞች ሆነን፣ እምነት እስከሚገለጥ ድረስ ተዘግቶብን ነበርን።

24. ስለዚህ በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያደርሰን ሞግዚታችን ሆነ።

25. አሁን ግን ያ እምነት ስለ መጣ፣ ከእንግዲህ በሕግ ሞግዚትነት ሥር አይደለንም።

የእግዚአብሔር ልጆች

26. ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ፤

27. ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁላችሁ ክርስቶስን ለብሳችሁታልና።

28. በአይሁድና በግሪክ፣ በባሪያና በነጻ ሰው፣ በወንድና በሴት መካከል ልዩነት የለም፤ ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ናችሁ።

29. የክርስቶስ ከሆናችሁ፣ እናንተ የአብርሃም ዘር ናችሁ፤ እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ።