ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕብራውያን 7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ካህኑ መልከጼዴቅ

1. ይህ መልከጼዴቅ የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበር፤ እርሱም አብርሃም ነገሥታትን ድል አድርጎ ሲመለስ አግኝቶት ባረከው፤

2. አብርሃምም ከሁሉ ነገር ዓሥራት አውጥቶ ሰጠው። በመጀመሪያ ስሙ “የጽድቅ ንጉሥ” ማለት ነው፤ ኋላም ደግሞ “የሳሌም ንጉሥ” ማለትም “የሰላም ንጉሥ ማለት” ነው።

3. አባትና እናት ወይም የትውልድ ሐረግ የለውም፤ ለዘመኑ መጀመሪያ፣ ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፤ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ልጅ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።

4. እስቲ እርሱ የቱን ያህል ታላቅ እንደሆነ ዐስቡ፤ ርእሰ አበው የሆነው አብርሃም እንኳ ካገኘው ምርኮ ዓሥራት አውጥቶ ሰጠው።

5. ክህነት የተሰጣቸው የሌዊ ልጆች ምንም እንኳ ወንድሞቻቸው የአብርሃም ዘሮች ቢሆኑም፣ ከሕዝቡ ማለት ከገዛ ወንድሞቻቸው ዓሥራት እንዲቀበሉ ሕጉ ያዛል።

6. ይህ ግን ትውልዱ ከሌዊ ወገን አይደለም፤ ይሁን እንጂ ከአብርሃም ዓሥራት ተቀበለ፤ የተስፋ ቃል የተቀበለውንም ባረከው።

7. ትንሹ በትልቁ እንደሚባረክ ጥርጥር የለውም።

8. በአንድ በኩል ዓሥራት የሚቀበሉት ሟች ሰዎች ናቸው፤ በሌላ በኩል ግን ሕያው ሆኖ እንደሚኖር የተመሰከረለት ይቀበላል።

9. እንዲያውም ዓሥራት የሚቀበለው ሌዊ፣ ራሱ በአብርሃም በኩል ዓሥራት ከፍሎአል ማለት ይቻላል፤

10. ምክንያቱም መልከጼዴቅ አብርሃምን ባገኘው ጊዜ፣ ሌዊ ገና በአባቱ በአብርሃም አብራክ ነበር።

ኢየሱስ እንደ መልከጼዴቅ

11. ፍጹምነት የተገኘውና ሕጉ ለሕዝቡ የተሰጠው በሌዊ ክህነት መሠረት ቢሆን ኖሮ፣ እንደ አሮን ሳይሆን እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ያለው ሌላ ካህን መምጣቱ ለምን አስፈለገ?

12. የክህነት ለውጥ ካለ ሕጉም ሊለወጥ ግድ ነውና።

13. ይህ ሁሉ የተነገረለት እርሱ ከሌላ ነገድ ነው፤ ከዚያም ነገድ በመሠዊያ ያገለገለ ማንም የለም።

14. ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደ መጣ ግልጽ ነውና፤ ሙሴ ስለ ካህናት ሲናገር ይህን ነገድ አስመልክቶ የተናገረው ምንም ነገር የለም።

15. እንደ መልከጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን ቢነሣ ግን እኛ የተናገርነው ይበልጥ ግልጽ ይሆናል፤

16. እርሱ ካህን የሆነው በማይጠፋ የሕይወት ኀይል መሠረት እንጂ፣ እንደ ትውልዱ የሕግ ሥርዐት አይደለም፤

17. እንዲህ ተብሎ ተመስክሮለታል፤“እንደ መልከጼዴቅ ሹመት፣አንተ ለዘላለም ካህን ነህ።”

18. የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና የማይጠቅም በመሆኑ ተሽሮአል፤

19. ሕጉ ማንንም ፍጹም ሊያደርግ ስለማይችል ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ መጥቶአል።

20. ይህ ያለ መሐላ አልሆነም፤ ሌሎች ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤

21. እርሱ ግን ካህን የሆነው በመሐላ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሮለታል፤“ጌታ ማለ፤ዐሳቡንም አይለውጥም፤‘አንተ ለዘላለም ካህን ነህ።’ ”

22. ከዚህ መሐላ የተነሣ፣ ኢየሱስ ለተሻለ ኪዳን ዋስ ሆኖአል።

23. በአገልግሎታቸው እንዳይቀጥሉ ሞት ስለ ከለከላቸው፣ የቀድሞዎቹ ካህናት ቍጥራቸው ብዙ ነበር፤

24. ኢየሱስ ግን ለዘላለም የሚኖር በመሆኑ፣ ክህነቱ የማይሻር ነው።

25. ስለዚህ ስለ እነርሱ እየማለደ ሁል ጊዜ በሕይወት ስለሚኖር፣ በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።

26. እንግዲህ ለእኛ የሚያስፈልገን፣ ቅዱስ፣ ነቀፋ የሌለበት፣ ንጹሕ፣ ከኀጢአተኞች የተለየና ከሰማያት በላይ የከበረ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ነው።

27. እርሱም እንደ ሌሎቹ ሊቃነ ካህናት፣ መጀመሪያ ስለ ራሱ ኀጢአት ከዚያም ስለ ሕዝቡ ኀጢአት በየቀኑ መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልገውም፤ ራሱን በሰጠ ጊዜ፣ ስለ ኀጢአታቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት አቅርቦአልና።

28. ሕጉ ደካማ የሆኑትን ሰዎች ሊቃነ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣው መሐላ ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ሾሞአል።