ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 7:18-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. ማንኛውም የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ በሦስተኛው ቀን ከተበላ ተቀባይነት የለውም፤ ርኵስ በመሆኑ ላቀረበው ሰው ዋጋ አይኖረውም፤ ከዚያም የበላ ሰው የበደል ዕዳ ይሆንበታል።

19. “ ‘ርኩስ ከሆነ ነገር ጋር የተነካካ ሥጋ ይቃጠል እንጂ አይበላ። ሌላውን ሥጋ ግን በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነ ማንኛውም ሰው ይብላ፤

20. ነገር ግን ንጹሕ ያልሆነ ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የቀረበውን የትኛውንም የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፣ ከሕዝቡ ፈጽሞ ይወገድ።

21. ማንኛውም ሰው የሰውን ርኵሰት ወይም ርኩስ እንስሳን ወይም ማንኛውንም ርኩስ ነገር ቢነካና ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከቀረበው የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፣ ያ ሰው ፈጽሞ ከሕዝቡ ይወገድ።

22. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

23. “ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘የበሬ ወይም የላም፣ የበግ ወይም የፍየል ሥብ አትብሉ።

24. ሞቶ የተገኘው ወይም አውሬ የገደለው ከብት ሥብ ለሌላ ተግባር ይዋል እንጂ አይበላ።

25. ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ከሚቀርብ እንስሳ ሥብ የሚበላ ማንኛውም ሰው ከሕዝቡ ይወገድ።

26. በየትኛውም ቦታ ብትኖሩ የማንኛውንም የወፍ ዘር ወይም የእንስሳ ደም አትብሉ።

27. ማንኛውም ሰው ደም ቢበላ፣ ያ ሰው ከሕዝቡ ይወገድ።’ ”

28. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

29. “ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘የኅብረት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያቀርብ ማንኛውም ሰው ስለ ራሱ መሥዋዕት አድርጎ ከዚሁ ላይ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያቅርብ።

30. በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቀርበውን መሥዋዕት በራሱ እጅ ያቅርበው፤ ሥቡን ከፍርምባው ጋር ያቅርብ፤ ፍርምባውን መሥዋዕት አድርጎ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይወዝውዘው።

31. ካህኑ ሥቡን በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ፍርምባው ግን ለአሮንና ለልጆቹ ይሰጥ።

32. የኅብረት መሥዋዕታችሁን የቀኝ ወርች ለካህኑ የተለየ አድርጋችሁ ስጡት።

33. የኅብረት መሥዋዕቱን ደምና ሥብ የሚያቀርበው የአሮን ልጅ ቀኝ ወርቹን የራሱ ድርሻ አድርጎ ይውሰድ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 7