ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የበደል መሥዋዕት

1. “ ‘እጅግ ቅዱስ የሆነው የበደል መሥዋዕት የአቀራረብ ሥርዐት ይህ ነው፦

2. የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የበደሉም መሥዋዕት እዚያው ይታረድ፤ ደሙም በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ይረጭ።

3. ሥቡን በሙሉ ያቅርብ፤ ይኸውም፦ ላቱን፣ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ፣

4. ሁለቱ ኵላሊቶች፣ በኵላሊቶቹ ላይና በጐድኑ አጠገብ ያለውን ሥብ እንዲሁም ከኵላሊቶቹ ጋር የሚወጣውን የጒበቱን ሽፋን አብሮ ያቅርብ።

5. ካህኑም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ይህም የበደል መሥዋዕት ነው።

6. ከካህን ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ከዚህ መብላት ይችላል፤ ነገር ግን በተቀደሰ ስፍራ ይበላ፤ ይህም እጅግ ቅዱስ ነው።

7. “ ‘የኀጢአት መሥዋዕትና የበደል መሥዋዕት አቀራረብ ሥርዐት አንድ ነው፤ መሥዋዕቶቹ የስርየቱን ሥርዐት ለሚያስ ፈጽመው ካህን ይሰጣሉ።

8. ስለማንኛውም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርበው ካህን ቈዳውን ለራሱ ይውሰድ።

9. በማብሰያ ምድጃ የተጋገረ፣ በመቀቀያ ወይም በምጣድ የበሰለ ማንኛውም የእህል ቊርባን ለሚያቀርበው ካህን ይሰጥ።

10. ማናቸውም በዘይት የተለወሰ ወይም ደረቅ የእህል ቊርባን ለአሮን ልጆች ሁሉ እኩል ይሰጥ።

የኅብረት መሥዋዕት

11. “ ‘አንድ ሰው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የኅብረት መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ፣ ሊከተለው የሚገባው ሥርዐት ይህ ነው፦

12. “ ‘መሥዋዕቱን የሚያቀርበው ለምስጋና መግለጫ ከሆነ፣ ከምስጋና መሥዋዕቱ ጋር ያለ እርሾ የተጋገረና በዘይት የተለወሰ ኅብስት እርሾ ሳይገባበት በሥቡ ተጋግሮ ዘይት የተቀባ ቂጣ በሚገባ ታሽቶ በዘይት የተለወሰም የላመ ዱቄት ኅብስት አብሮ ያቅርብ።

13. ለምስጋና ከሚሆነው የኅብረት መሥዋዕት ጋር በእርሾ የተጋገረ ኅብስት ያቅርብ።

14. ከእያንዳንዱም ዐይነት አንዳንድ አንሥቶ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተለየ ቊርባን በማድረግ ያቅርብ፤ ይህም የኅብረት መሥዋዕቱን ደም ለሚረጨው ካህን ይሰጥ።

15. ለምስጋና የሚሆነው የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ፣ በቀረበበት ዕለት ይበላ እንጂ አንዳች አይደር።

16. “ ‘መሥዋዕቱ ስእለት በመፈጸሙ ወይም በበጎ ፈቃድ የሚቀርብ ከሆነ፣ በቀረበበት ዕለት ይበላ፤ የተረፈውም ሁሉ በማግስቱ ይበላ።

17. እስከ ሦስት ቀን የቆየ ማንኛውም የመሥዋዕቱ ሥጋ ይቃጠል።

18. ማንኛውም የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ በሦስተኛው ቀን ከተበላ ተቀባይነት የለውም፤ ርኵስ በመሆኑ ላቀረበው ሰው ዋጋ አይኖረውም፤ ከዚያም የበላ ሰው የበደል ዕዳ ይሆንበታል።

19. “ ‘ርኩስ ከሆነ ነገር ጋር የተነካካ ሥጋ ይቃጠል እንጂ አይበላ። ሌላውን ሥጋ ግን በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነ ማንኛውም ሰው ይብላ፤

20. ነገር ግን ንጹሕ ያልሆነ ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የቀረበውን የትኛውንም የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፣ ከሕዝቡ ፈጽሞ ይወገድ።

21. ማንኛውም ሰው የሰውን ርኵሰት ወይም ርኩስ እንስሳን ወይም ማንኛውንም ርኩስ ነገር ቢነካና ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከቀረበው የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፣ ያ ሰው ፈጽሞ ከሕዝቡ ይወገድ።

ሥብና ደም መብላት መከልከሉ

22. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

23. “ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘የበሬ ወይም የላም፣ የበግ ወይም የፍየል ሥብ አትብሉ።

24. ሞቶ የተገኘው ወይም አውሬ የገደለው ከብት ሥብ ለሌላ ተግባር ይዋል እንጂ አይበላ።

25. ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ከሚቀርብ እንስሳ ሥብ የሚበላ ማንኛውም ሰው ከሕዝቡ ይወገድ።

26. በየትኛውም ቦታ ብትኖሩ የማንኛውንም የወፍ ዘር ወይም የእንስሳ ደም አትብሉ።

27. ማንኛውም ሰው ደም ቢበላ፣ ያ ሰው ከሕዝቡ ይወገድ።’ ”

የካህኑ ድርሻ

28. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

29. “ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘የኅብረት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያቀርብ ማንኛውም ሰው ስለ ራሱ መሥዋዕት አድርጎ ከዚሁ ላይ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያቅርብ።

30. በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቀርበውን መሥዋዕት በራሱ እጅ ያቅርበው፤ ሥቡን ከፍርምባው ጋር ያቅርብ፤ ፍርምባውን መሥዋዕት አድርጎ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይወዝውዘው።

31. ካህኑ ሥቡን በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ፍርምባው ግን ለአሮንና ለልጆቹ ይሰጥ።

32. የኅብረት መሥዋዕታችሁን የቀኝ ወርች ለካህኑ የተለየ አድርጋችሁ ስጡት።

33. የኅብረት መሥዋዕቱን ደምና ሥብ የሚያቀርበው የአሮን ልጅ ቀኝ ወርቹን የራሱ ድርሻ አድርጎ ይውሰድ።

34. ከእስራኤላውያን የኅብረት መሥዋዕት ላይ የተወዘወዘውን ፍርምባና የቀረበውን ወርች ወስጃለሁ፤ ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹም ከእስራኤላውያን የሚያገኙት መደበኛ ድርሻቸው እንዲሆን ሰጥቻቸዋለሁ።’ ”

35. ካህናት ሆነው እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲያገለግሉ በቀረቡ ቀን፣ በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከቀረበው መሥዋዕት ላይ ለአሮንና ለልጆቹ የተመደበላቸው ድርሻ ይህ ነው።

36. ካህናቱ በተቀቡበት ቀን፣ እስራኤላውያን መደበኛ ድርሻ አድርገው ከትውልድ እስከ ትውልድ ይህን እንዲሰጧቸው እግዚአብሔር (ያህዌ) አዘዘ።

37. እንግዲህ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የእህል ቊርባን፣ የኀጢአት መሥዋዕት፣ የበደል መሥዋዕት፣ የክህነት ሹመት መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት ሥርዐት ይህ ነው፤

38. ይህም፣ በሲና ምድረ በዳ እስራኤላውያን መሥዋዕታቸውን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲያቀርቡ ባዘዛቸው ቀን በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ የሰጠው ሥርዐት ነው።