ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ገላትያ 3:7-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. እንግዲህ እነዚያ የሚያምኑት የአብርሃም ልጆች እንደሆኑ አስተውሉ።

8. መጽሐፍ፣ እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቅ አስቀድሞ በማየት፣ “አሕዛብ ሁሉ በአንተ ይባረካሉ” በማለት ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ አስታወቀው።

9. ስለዚህ በእምነት የሆኑት፣ የእምነት ሰው ከሆነው ከአብርሃም ጋር ቡሩካን ናቸው።

10. ሕግን በመጠበቅ የሚተማመኑ ሁሉ ከርግማን በታች ናቸው፤ “በሕግ መጻሕፍት የተጻፈውን ሁሉ የማያደርግ የተረገመ ነው” ተብሎ ተጽፎአልና።

11. “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ስለ ተባለ፣ ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንደማይጸድቅ ግልጽ ነው።

12. ሕግ በእምነት ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ ነገር ግን “ሕግጋትን የሚፈጽም ሰው በእነርሱ በሕይወት ይኖራል” ተብሎአል።

13. “በዕንጨት ላይ የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ስለ ተጻፈ፣ ክርስቶስ ስለ እኛ ርግማን ሆኖ ከሕግ ርግማን ዋጅቶናል፤

14. ለአብርሃም የተሰጠው በረከት፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ለአሕዛብ እንዲደርስ ዋጅቶናል፤ ይኸውም በእምነት የመንፈስን ተስፋ እንድንቀበል ነው።

15. ወንድሞች ሆይ፤ ከሰው ዕለታዊ ሕይወት የተለመደውን ምሳሌ አድርጌ ላቅርብ፤ የሰው ኪዳን እንኳ አንድ ጊዜ ከጸደቀ በኋላ ማንም ሊሽረው ወይም በእርሱ ላይ ሊጨምርበት እንደማይችል ሁሉ፣ በዚህም ጒዳይ ቢሆን እንደዚሁ ነው።

16. የተስፋውም ቃል የተነገረው ለአብርሃምና ለዘሩ ነበር፤ መጽሐፍ፣ ለብዙ ሰዎች እንደሚነገር፣ “ለዘሮቹ” አይልም፤ ነገር ግን ለአንድ ሰው እንደሚነገር፣ “ለዘርህ” ይላል፤ እርሱም ክርስቶስ ነው።

17. የምለው እንዲህ ነው፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ፣ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የጸናውን ኪዳን አፍርሶ የተስፋውን ቃል አይሽርም።

18. ርስትን መውረስ በሕግ ቢሆን ኖሮ፣ በተስፋ ቃል ባልተገኘ ነበርና፤ እግዚአብሔር ግን በጸጋው በተስፋ ቃል አማካይነት ለአብርሃም ሰጥቶታል።

19. ታዲያ ሕግ የተሰጠበት ምክንያት ምንድን ነው? ሕግ የተጨመረው ከመተላለፍ የተነሣ ተስፋው ያመለከተው ዘር እስኪመጣ ድረስ ነበር፤ ሕጉም የመጣው በመላእክት በኩል፣ በአንድ መካከለኛ እጅ ነበር።

20. ሆኖም መካከለኛው አንድን ወገን ብቻ የሚወክል አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ገላትያ 3