ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ገላትያ 1:7-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. እንደ እውነቱ ከሆነ ሌላ ወንጌል የለም። የሚያደነጋግሯችሁና የክርስቶስን ወንጌል ለማጣመም ጥረት የሚያደርጉ አንዳንድ ሰዎች አሉ።

8. ነገር ግን እኛም ብንሆን ወይም የሰማይ መልአክ፣ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ እርሱ ለዘላለም የተረገመ ይሁን።

9. ቀደም ብለን እንዳልነው፣ አሁንም ደግሜ እላለሁ፤ ማንም ከተቀበላችሁት ሌላ የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ፣ እርሱ ለዘላለም የተረገመ ይሁን።

10. አሁን እኔ ጐሽ ለመባል የምሻው በሰዎች ዘንድ ነው ወይስ በእግዚአብሔር ዘንድ? ወይስ ሰዎችን ደስ ለማሰኘት እየተጣጣርሁ ነው? ሰዎችን ደስ ለማሰኘት የምጥር ብሆን ኖሮ፣ የክርስቶስ አገልጋይ ባልሆንሁ ነበር።

11. ወንድሞች ሆይ፤ የሰበክሁላችሁ ወንጌል ሰው ሠራሽ አለመሆኑን እንድታውቁ እፈልጋለሁ፤

12. ከማንም ሰው አልተቀበልሁትም፤ ከማንም አልተማርሁትም፤ ይልቁንስ በመገለጥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ተቀበልሁት።

13. ቀድሞ በአይሁድ ሃይማኖት እንዴት እንደኖርሁ፣ የእግዚአብሔርንም ቤተ ክርስቲያን እንዴት በእጅጉ እንዳሳደድሁ፣ ለማጥፋትም እንዴት እንደጣርሁ ሰምታችኋል፤

14. በእኔ ዕድሜ ዘመን ከነበሩት ከብዙዎቹ አይሁድ ይበልጥ በአይሁድ ሃይማኖት እልቅ ነበር፤ ስለ አባቶቼም ወግ እጅግ ቀናተኛ ነበርሁ።

15. ነገር ግን፣ ከእናቴ ማሕፀን ጀምሮ የለየኝና በጸጋው የጠራኝ እግዚአብሔር፣

16. በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ እንድሰብክ ልጁን በእኔ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፣ ከማንም ሥጋ ለባሽ ጋር አልተማከርሁም፤

17. ከእኔ በፊት ሐዋርያት ወደ ሆኑትም ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፤ ነገር ግን ወዲያው ወደ ዐረብ አገር ሄድሁ፤ በኋላም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ።

18. ከዚያም ከሦስት ዓመት በኋላ፣ ጴጥሮስን አገኘው ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፤ ከእርሱም ጋር ዐሥራ አምስት ቀን ተቀመጥሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ገላትያ 1