ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 8:8-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. እንደ ገናም ጎንበስ ብሎ በምድር ላይ ጻፈ።

9. ይህን እንደ ሰሙ፣ ከሽማግሌዎች ጀምሮ አንድ በአንድ ወጡ፤ ሴትዮዋም እዚያው ፊቱ እንደ ቆመች ኢየሱስ ብቻውን ቀረ።

10. ኢየሱስም ቀና ብሎ፣ “አንቺ ሴት፣ ሰዎቹ የት ሄዱ? የፈረደብሽ የለምን?” አላት።

11. እርሷም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንድም የለም” አለች።ኢየሱስም፣ “እኔም አልፈርድብሽም፤ በይ ሂጂ፤ ከእንግዲህ ግን ኀጢአት አትሥሪ” አላት።

12. ኢየሱስ እንደ ገና ለሰዎቹ፣ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝም የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ ከቶ በጨለማ አይመላለስም” አላቸው።

13. ፈሪሳውያንም፣ “አንተ ስለ ራስህ ስለምት መሰክር፣ ምስክርነትህ ተቀባይነት የለውም” አሉት።

14. ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ከየት እንደ መጣሁና ወዴት እንደምሄድ ስለማውቅ ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከየት እንደ መጣሁ ወይም ወዴት እንደምሄድ የምታውቁት ነገር የለም።

15. እናንተ እንደ ሰው አስተሳሰብ ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በማንም አልፈርድም፤

16. ብፈርድም፣ ከላከኝ ከአብ ጋር እንጂ ብቻዬን ስላልሆንሁ ፍርዴ ትክክል ነው።

17. የሁለት ሰዎች ምስክርነት ተቀባይነት እንዳለው በሕጋችሁ ተጽፎአል።

18. ስለ ራሴ የምመሰክር አንዱ እኔ ነኝ፤ ሌላውም ምስክሬ የላከኝ አብ ነው።”

19. ከዚያም፣ “አባትህ የት ነው?” አሉት።ኢየሱስም፣ “አባቴንም እኔንም አታውቁም፤ እኔን ብታውቁኝ ኖሮ፣ አባቴንም ባወቃችሁ ነበር” ሲል መለሰላቸው።

20. ኢየሱስ ይህን የተናገረው በቤተ መቅደሱ ግቢ፣ በግምጃ ቤት አጠገብ ሲያስተምር ነበር፤ ይሁን እንጂ ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም አልያዘውም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 8