ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 8:44-55 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

44. እናንተ የአባታችሁ የዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ፍላጎት ለመፈጸም ትሻላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበር፤ በእርሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት አልጸናም፤ እርሱ ሐሰተኛ፣ የሐሰትም አባት በመሆኑ ሐሰትን ሲናገር፣ የሚናገረው ከራሱ አፍልቆ ነው፤

45. እኔ ግን እውነት ስለምናገር አታምኑኝም።

46. ከእናንተ ስለ ኀጢአት በማስረጃ ሊከሰኝ የሚችል አለን? እውነት የምናገር ከሆነ፣ ለምን አታምኑኝም?

47. ከእግዚአብሔር የሆነ እግዚአብሔር የሚለውን ይሰማል፤ እናንተ ግን ከእግዚአብሔር ስላልሆናችሁ አትሰሙም።”

48. አይሁድም መልሰው፣ “አንተ ሳምራዊ ነህ፤ ደግሞም ጋኔን አድሮብሃል ማለታችን ትክክል አይደለምን?” አሉት።

49. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔስ አባቴን አከብረዋለሁ እንጂ ጋኔን አላደረብኝም፤ እናንተ ግን ታዋርዱኛላችሁ።

50. እኔ የራሴን ክብር አልፈልግም፤ የሚፈልግ ግን አለ፤ ፈራጁም እርሱ ነው።

51. እውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ቃሌን ቢጠብቅ፣ ሞትን ፈጽሞ አያይም።”

52. አይሁድም እንዲህ አሉት፤ “ጋኔን እንዳለብህ አሁን ዐወቅን፤ አብርሃም ሞተ፤ ነቢያትም እንዲሁ፤ አንተ ግን ማንም ቃልህን ቢጠብቅ ሞትን ፈጽሞ እንደማይቀምስ ትናገራለህ።

53. አንተ ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህን? እርሱ ሞተ፤ ነቢያቱም እንዲሁ፤ ለመሆኑ አንተ ማን ነኝ ልትል ነው?”

54. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ ራሴን ባከብር፣ ክብሬ ከንቱ ነው፤ የሚያከብረኝ ግን እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው።

55. እናንተ ባታውቁትም እኔ ዐውቀዋለሁ፤ አላውቀውም ብል፣ እኔም እንደ እናንተው ሐሰተኛ እሆናለሁ። እኔ ግን ዐውቀዋለሁ፤ ቃሉንም እጠብቃለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 8