ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 8:28-42 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

28. ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የሰው ልጅን ከፍ ከፍ ባደረጋችሁት ጊዜ፣ ያ ያልሁት እርሱ እኔ እንደሆንሁና አብ ያስተማረኝን እንደምናገር፣ በራሴም ፈቃድ ምንም እንደማላደርግ ታውቃላችሁ፤

29. የላከኝ እርሱ ከእኔ ጋር ነው፤ ምንጊዜም የሚያስደስተውን ስለማደርግ ብቻዬን አልተወኝም።”

30. ይህንም እንደ ተናገረ ብዙዎች በእርሱ አመኑ።

31. ኢየሱስም በእርሱ ያመኑትን አይሁድ እንዲህ አላቸው፤ “በትምህርቴ ብትጸኑ እናንተ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤

32. እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል።”

33. እነርሱም መልሰው፣ “እኛ የአብርሃም ልጆች ነን፤ ለማንም ባሪያዎች ሆነን አናውቅም፤ ታዲያ፣ ‘ነጻ ትወጣላችሁ’ እንዴት ትለናለህ?” አሉት።

34. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ኀጢአት የሚያደርግ የኀጢአት ባሪያ ነው፤

35. ባሪያ ለዘለቄታ በቤተ ሰቡ ውስጥ አይኖርም፤ ልጅ ግን ምንጊዜም በቤት ይኖራል።

36. እንግዲህ ወልድ ነጻ ካወጣችሁ፣ በእውነት ነጻ ትሆናላችሁ።

37. የአብርሃም ልጆች መሆናችሁን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ቃሌን ስለማትቀበሉ ልትገድሉኝ ቈርጣችሁ ተነሥታችኋል።

38. እኔ በአባቴ ዘንድ ያየሁትን እናገራለሁ፤ እናንተም ከአባታችሁ የሰማችሁትን ታደርጋላችሁ።”

39. እነርሱም፣ “አባታችንስ አብርሃም ነው” ብለው መለሱለት።ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የአብርሃም ልጆችስ ብትሆኑ፣ አብርሃም የሠራውን ትሠሩ ነበር።

40. ከእግዚአብሔር ሰምቼ እውነቱን የነገርኋችሁን እኔን ለመግደል ቈርጣችሁ ተነሥታችኋል፤ አብርሃም ግን እንዲህ አላደረገም።

41. እናንተ የምታደርጉት አባታችሁ የሚያደርገውን ነው።”እነርሱም፣ “እኛስ በዝሙት የተወለድን አይደለንም፤ አባታችንም አንዱ እግዚአብሔር ብቻ ነው” ሲሉ መለሱለት።

42. ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር አባታችሁ ቢሆን ኖሮ፣ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፣ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እርሱ ላከኝ እንጂ በገዛ ራሴ አልመጣሁም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 8