ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 8:22-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. አይሁድም፣ “ ‘እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም’ ያለው ራሱን ሊገድል ይሆን?” አሉ።

23. እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ከታች ናችሁ፤ እኔ ከላይ ነኝ፤ እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፤ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም።

24. በኀጢአታችሁ እንደምትሞቱ ነግሬአችኋለሁ፤ እኔ እርሱ ነኝ ስላችሁ እኔ እርሱ እንደሆንሁ ካላመናችሁ፣ በኀጢአታችሁ ትሞታላችሁና።”

25. እነርሱም፣ “ለመሆኑ፣ አንተ ማን ነህ?” አሉት።ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እስካሁን የነገርኋችሁ እኔ እርሱ ነኝ፤

26. በእናንተ ላይ ብዙ የምናገረውና ብዙ የምፈርደው ነገር አለኝ፤ ዳሩ ግን የላከኝ ታማኝ ነው፤ ከእርሱም የሰማሁትን ለዓለም እናገራለሁ።”

27. እነርሱም ስለ አብ እየነገራቸው እንደ ነበር አላስተዋሉም።

28. ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የሰው ልጅን ከፍ ከፍ ባደረጋችሁት ጊዜ፣ ያ ያልሁት እርሱ እኔ እንደሆንሁና አብ ያስተማረኝን እንደምናገር፣ በራሴም ፈቃድ ምንም እንደማላደርግ ታውቃላችሁ፤

29. የላከኝ እርሱ ከእኔ ጋር ነው፤ ምንጊዜም የሚያስደስተውን ስለማደርግ ብቻዬን አልተወኝም።”

30. ይህንም እንደ ተናገረ ብዙዎች በእርሱ አመኑ።

31. ኢየሱስም በእርሱ ያመኑትን አይሁድ እንዲህ አላቸው፤ “በትምህርቴ ብትጸኑ እናንተ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤

32. እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል።”

33. እነርሱም መልሰው፣ “እኛ የአብርሃም ልጆች ነን፤ ለማንም ባሪያዎች ሆነን አናውቅም፤ ታዲያ፣ ‘ነጻ ትወጣላችሁ’ እንዴት ትለናለህ?” አሉት።

34. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ኀጢአት የሚያደርግ የኀጢአት ባሪያ ነው፤

35. ባሪያ ለዘለቄታ በቤተ ሰቡ ውስጥ አይኖርም፤ ልጅ ግን ምንጊዜም በቤት ይኖራል።

36. እንግዲህ ወልድ ነጻ ካወጣችሁ፣ በእውነት ነጻ ትሆናላችሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 8