ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 7:23-39 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

23. የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሕፃን በሰንበት የሚገረዝ ከሆነ፣ የሰውን ሁለንተና በሰንበት ስለ ፈወስሁ ለምን በእኔ ላይ ትቈጣላችሁ?

24. የሰውን ፊት በማየት መፍረድ ትታችሁ ቅን ፍርድ ፍረዱ።”

25. በዚህ ጊዜ በኢየሩሳሌም የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ አሉ፤ “ሊገድሉት የሚፈልጉት ሰው ይህ አይደለምን?

26. ይኸው እርሱ በአደባባይ ይናገራል፤ አንድም ቃል አይናገሩትም፤ ክርስቶስ ነው ብለው ባለ ሥልጣኖቹም ተቀብለውት ይሆን?

27. ይህ ሰው ግን ከየት እንደሆነ እኛ እናውቃለን፤ ክርስቶስ ሲመጣ እኮ ከየት እንደሆነ ማንም አያውቅም።”

28. ኢየሱስ በቤተ መቅደስ አደባባይ ሲያስተምር ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “አዎን፣ እኔን ታውቁኛላችሁ፤ ከየት እንደሆንሁም ታውቃላችሁ። እኔ እዚህ ያለሁት በገዛ ራሴ አይደለም፤ ነገር ግን የላከኝ እርሱ እውነተኛ ነው። እናንተ አታውቁትም፤

29. እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ስለ ሆንሁ፣ እርሱም ስለ ላከኝ ዐውቀዋለሁ።”

30. ስለዚህ ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አላሳረፈበትም፤

31. ሆኖም ከሕዝቡ ብዙዎች በእርሱ አምነው፣ “ታዲያ፣ ክርስቶስ ሲመጣ ይህ ሰው ከሚሠራቸው ታምራዊ ምልክቶች የበለጠ ያደርጋል?” አሉ።

32. ፈሪሳውያን፣ ሕዝቡ ስለ እርሱ በጒምጒ ምታ የሚነጋገረውን ነገር ሰሙ፤ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም እንዲይዙት የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችን ላኳቸው።

33. ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ከእናንተ ጋር የምቈየው ጥቂት ጊዜ ነው፤ ከዚያም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፤

34. ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤ ወዳለሁበትም ልትመጡ አትችሉም።”

35. አይሁድም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “ይህ ሰው፣ ልናገኘው የማንችለው ወዴት ለመሄድ ቢያስብ ነው? በግሪኮች መካከል ተበታትነው ወደሚኖሩት ወገኖቻችን ሄዶ ግሪኮችን ሊያስተምር ፈልጎ ይሆን?

36. ‘ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤’ ደግሞም፣ ‘እኔ ወዳለሁበት ልትመጡ አትችሉም’ ሲል ምን ማለቱ ይሆን?”

37. የበዓሉ መጨረሻ በሆነው በታላቁ ቀን፣ ኢየሱስ ቆሞ ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ አለ፤ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፤

38. በእኔ የሚያምን፣ መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውሃ ምንጭ ከውስጡ ይፈልቃል።”

39. ይህን ያለው በእርሱ የሚያምኑ ስለሚቀ በሉት መንፈስ ነበር፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ አልተሰጠም ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 7