ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 4:46-54 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

46. ኢየሱስም ውሃውን የወይን ጠጅ ወዳደ ረገበት፣ በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ቃና ከተማ ዳግመኛ መጣ፤ በቅፍርናሆምም ልጁ የታመመበት አንድ የቤተ መንግሥት ሹም ነበረ፤

47. ይህም ሰው ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መምጣቱን በሰማ ጊዜ፣ ወደ እርሱ ሄደና በሞት አፋፍ ላይ የነበረውን ልጁን መጥቶ እንዲፈውስለት ለመነው።

48. ኢየሱስም፣ “መቼውንም እናንተ ምልክቶችንና ድንቅ ነገሮችን ካላያችሁ አታምኑም” አለው።

49. ሹሙም፣ “ጌታዬ፤ ልጄ ከመሞቱ በፊት እባክህ ድረስልኝ” አለው።

50. ኢየሱስም፣ “ልጅህ በሕይወት ይኖራልና ሂድ” አለው።ሰውየውም ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አምኖ ሄደ፤

51. በመንገድ ላይ እንዳለም፣ አገልጋዮቹ አግኝተውት ልጁ በሕይወት መኖሩን ነገሩት።

52. እርሱም ልጁ በስንት ሰዓት እንደ ተሻለው ሲጠይቃቸው፣ “ትኵሳቱ የለቀቀው ትናንት በሰባት ሰዓት ላይ ነው” አሉት።

53. አባትዮውም ሰዓቱ ኢየሱስ፣ “ልጅህ በሕይወት ይኖራል” ያለበት ሰዓት መሆኑን ተገነዘበ፤ እርሱና ቤተ ሰቡም ሁሉ አመኑ።

54. ይህም፣ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛው ታምራዊ ምልክት ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 4