ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 4:22-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. እናንተ ሳምራውያን ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ ግን ድነት ከአይሁድ ስለ ሆነ ለምናውቀው እንሰግዳለን።

23. በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቶአል፤ አብም እንደዚህ በእውነት የሚሰግዱለትን ይፈልጋል።

24. እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል።”

25. ሴትዮዋም፣ “ክርስቶስ የተባለ መሲሕ እንደሚመጣ ዐውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ነገር ይነግረናል” አለችው።

26. ኢየሱስም፣ “የማነጋግርሽ እኮ እኔ እርሱ ነኝ” ሲል ገልጦ ነገራት።

27. በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው መጡ፤ ከሴት ጋር ሲነጋገር በማግኘታቸው ተደነቁ፤ ሆኖም ግን፤ “ምን ፈለግህ?” ወይም፣ “ከእርሷ ጋር የምትነጋገረው ለምንድን ነው?” ብሎ የጠየቀው ማንም አልነበረም።

28. ሴትዮዋም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ተመለሰች፤ ለሕዝቡም፣

29. “ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እርሱ ክርስቶስ ይሆን እንዴ?” አለች፤

30. እነርሱም ከከተማ ወጥተው እርሱ ወዳለበት አመሩ።

31. በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ፣ “ረቢ፣ እህል ቅመስ እንጂ” አሉት።

32. እርሱ ግን፣ “እናንተ የማታውቁት፣ የምበላው ምግብ አለኝ” አላቸው።

33. ደቀ መዛሙርቱም፣ “ሰው ምግብ አምጥቶለት ይሆን እንዴ?” ተባባሉ።

34. ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው፤

35. እናንተ፣ ‘ከአራት ወር በኋላ መከር ይደርሳል’ ትሉ የለምን? እነሆ፣ አዝመራው ለመከር እንደ ደረሰ ቀና ብላችሁ ማሳውን ተመልከቱ እላችኋለሁ።

36. አጫጁ አሁንም ቢሆን እንኳ ደመወዙን እየተቀበለ ነው፤ ለዘላለም ሕይወት ይሆን ዘንድ አዝመራውን ይሰበስባል፤ ይህም ዘሪውና አጫጁ በጋራ ደስ እንዲላቸው ነው።

37. ስለዚህ፣ ‘አንዱ ይዘራል፤ ሌላውም ያጭዳል’ የተባለው ምሳሌ እውነት ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 4