ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 20:23-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

23. የሰዎችን ኀጢአት ይቅር ብትሉ፣ ኀጢአታቸው ይቅር ይባልላቸዋል፤ ኀጢአታቸውን ይቅር ባትሉ ግን፣ ይቅር አይባልላቸውም።”

24. በዚህ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው፣ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፣ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አልነበረም።

25. ሌሎች ደቀ መዛሙርትም፣ “ጌታን አየነው እኮ!” አሉት።እርሱ ግን፣ “በምስማር የተቸነከሩትን የእጆቹን ምልክቶች ካላየሁ፣ ምስማሮቹ በነበሩበት ቦታ ጣቴን ካላደረግሁ፣ በጐኑም እጄን ካላስገባሁ አላምንም” አለ።

26. ከስምንት ቀን በኋላም፣ ደቀ መዛሙርቱ በቤት ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበር፤ በሮቹ ተቈልፈው ነበር፤ ኢየሱስ ግን መጥቶ በመካከላቸው ቆመና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው።

27. ከዚያም ቶማስን፣ “ጣትህን ወደዚህ አምጣ፤ እጆቼንም ተመልከት፤ እጅህን ዘርጋና በጐኔ አስገባ፤ አትጠራጠር፤ እመን” አለው።

28. ቶማስም፣ “ጌታዬ፤ አምላኬም!” አለው።

29. ኢየሱስም፣ “አንተ ስላየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ግን ብፁዓን ናቸው” አለው።

30. ኢየሱስ በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፉ ሌሎች አያሌ ታምራዊ ምልክቶችን በደቀ መዛሙርቱ ፊት አድርጓል፤

31. ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ፣ አምናችሁም በስሙ ሕይወት እንዲኖራችሁ ይህ ተጽፎአል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 20