ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 16:20-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ታዝናላችሁም፤ ዓለም ግን ሐሤት ያደርጋል፤ ይሁን እንጂ ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል።

21. ሴት ቀኗ ደርሶ ስትወልድ ትጨነቃለች፤ ከተገላገለች በኋላ ግን፣ ሰው ወደ ዓለም ስለ መጣ ጭንቋን ትረሳለች፤

22. ለእናንተም እንደዚሁ አሁን የሐዘን ጊዜ ነው፤ ሆኖም እንደ ገና ስለማያችሁ ደስ ይላችኋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም።

23. በዚያ ቀን ከእኔ ምንም አትለምኑም፤ እውነት እላችኋለሁ፤ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል።

24. እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ለምኑ ትቀበላላችሁ፤ ደስታችሁም ሙሉ ይሆናል።

25. “እስከ አሁን የነገርኋችሁ በምሳሌ ቢሆንም እንኳ፣ ከእንግዲህ ግን ስለ አብ በምሳሌ ሳይሆን በግልጽ የምናገርበት ጊዜ ይመጣል።

26. በዚያ ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ ይህም በእናንተ ፈንታ አብን እለምናለሁ ማለቴ አይደለም፤

27. ስለ ወደዳችሁኝና ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ ራሱ ይወዳችኋል።

28. ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ አሁን ግን ዓለምን ትቼ ወደ አብ እሄዳለሁ።”

29. ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አሉ፤ “አሁንም እኮ ያለ ምሳሌ በግልጽ እየተናገርህ ነው።

30. አሁን ሁሉን ነገር እንደምታ ውቅና ማንም ሊጠይቅህ እንደማያስፈልግ ተረድተናል፤ ይህም ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እንድናምን አድርጎናል።”

31. ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንስ አመናችሁ ማለት ነው?

32. እነሆ፤ ሁላችሁም በየፊናችሁ የምትበታተኑበት ጊዜ ይመጣል፤ ያም ጊዜ አሁን ነው። እኔንም ብቻዬን ትተዉኛላችሁ፤ ይሁን እንጂ አባቴ ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም።

33. “በእኔ ሰላም እንዲኖራችሁ፣ ይህን ነግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 16