ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 12:34-50 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

34. ሕዝቡም፣ “እኛስ ክርስቶስ ለዘላለም እንደሚኖር ከሕግ ሰምተናል፤ ታዲያ፣ ‘የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ማለት አለበት’ እንዴት ትላለህ? ይህስ ‘የሰው ልጅ’ ማን ነው?” አሉት።

35. ኢየሱስም እንዲህ ሲል ተናገራቸው፤ “ከእንግዲህ ለጥቂት ጊዜ ብርሃን አለላችሁ፤ ጨለማ ሳይመጣባችሁ፣ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማ የሚመላለስ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም።

36. የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በዚህ ብርሃን እመኑ።” ኢየሱስ ይህን ተናግሮ እንደ ጨረሰ ተለያቸው፤ ተሰወረባቸውም።

37. ኢየሱስ እነዚህን ታምራዊ ምልክቶች ሁሉ በፊታቸው ቢያደርግም እንኳ፣ አሁንም አላመኑበትም፤

38. ይኸውም ነቢዩ ኢሳይያስ፣“ጌታ ሆይ፤ ምስክርነታችንን ማን አመነ?የጌታ ክንድስ ለማን ተገለጠ?” ያለው ቃል እንዲፈጸም ነው።

39. ስለዚህ ማመን አልቻሉም፤ ይህም ኢሳይያስ በሌላ ቦታ እንዲህ ሲል እንደ ተናገረው ነው፤

40. “ዐይናቸውን አሳውሮአል፤ልባቸውንም አደንድኖአል፤ስለዚህ በዐይናቸው አያዩም፤በልባቸውም አያስተውሉም፤እንዳልፈውሳቸውም አይመለሱም።”

41. ኢሳይያስ ይህን ያለው የኢየሱስን ክብር ስላየ ነው፤ ስለ እርሱም ተናገረ።

42. ይህም ቢሆን፣ ከአለቆች መካከል እንኳ ሳይቀር ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ይሁን እንጂ ፈሪሳውያን ከምኵራብ እንዳያስወጧቸው ስለ ፈሩ ማመናቸውን አይገልጡም ነበር።

43. ይህም የሆነው በእግዚአብሔር ከመመስገን ይልቅ በሰው መመስገንን ስለ ወደዱ ነው።

44. ከዚያም ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “ማንም በእኔ ቢያምን በእኔ ብቻ ሳይሆን በላከኝም ማመኑ ነው፤

45. እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል።

46. በእኔ የሚያምን በጨለማ እንዳይኖር ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ።

47. “ቃሌን ሰምቶ በማይፈጽመው ላይ የምፈርደው እኔ አይደለሁም፤ ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ላይ ልፈርድ አልመጣሁምና።

48. በማይቀበለኝና ቃሌን በሚያቃልል ላይ የሚፈርድበት አለ፤ የተናገርሁት ቃል ራሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል፤ ምክንያቱም

49. እኔ ከራሴ አልተናገርሁም፤ ነገር ግን የላከኝ አብ ምን እንደምናገርና እንዴት እንደምናገር አዘዘኝ።

50. የእርሱ ትእዛዝ ወደ ዘላለም ሕይወት እንደሚያደርስ ዐውቃለሁ፤ ስለዚህም የምለው ሁሉ አብ እንድናገረው የነገረኝን ብቻ ነው።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 12