ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 12:25-38 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

25. ሕይወቱን የሚወድ ያጣታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን የሚጠላ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል።

26. የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፤ እኔም ባለሁበት አገልጋዬም በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝንም አባቴ ያከብረዋል።

27. “አሁንስ ነፍሴ ተጨነቀች፤ ምን ልበል? አባት ሆይ፤ ከዚች ሰዓት ታድነኝ? የለም፤ ይሁን የመጣሁት ለዚህች ሰዓት ነውና።

28. አባት ሆይ፤ ስምህን አክብረው።”ከዚያም፣ “አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ።

29. በዚያ የነበሩት፣ ድምፁን የሰሙት አያሌ ሰዎች፣ “ነጐድጓድ ነው” አሉ፤ ሌሎች ደግሞ፣ “መልአክ ተናገረው” አሉ።

30. ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ይህ ድምፅ የመጣው ስለ እኔ ሳይሆን ስለ እናንተ ነው፤

31. ይህ ዓለም የሚፈረድበት ጊዜ አሁን ነው፤ የዚህም ዓለም ገዥ አሁን ወደ ውጭ ይጣላል።

32. እኔ ግን ከምድር ከፍ ከፍ ባልሁ ጊዜ ሰውን ሁሉ ወደ ራሴ እስባለሁ።”

33. ይህን የተናገረው በምን ዐይነት ሞት እንደሚሞት ለማመልከት ነበር።

34. ሕዝቡም፣ “እኛስ ክርስቶስ ለዘላለም እንደሚኖር ከሕግ ሰምተናል፤ ታዲያ፣ ‘የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ማለት አለበት’ እንዴት ትላለህ? ይህስ ‘የሰው ልጅ’ ማን ነው?” አሉት።

35. ኢየሱስም እንዲህ ሲል ተናገራቸው፤ “ከእንግዲህ ለጥቂት ጊዜ ብርሃን አለላችሁ፤ ጨለማ ሳይመጣባችሁ፣ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማ የሚመላለስ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም።

36. የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በዚህ ብርሃን እመኑ።” ኢየሱስ ይህን ተናግሮ እንደ ጨረሰ ተለያቸው፤ ተሰወረባቸውም።

37. ኢየሱስ እነዚህን ታምራዊ ምልክቶች ሁሉ በፊታቸው ቢያደርግም እንኳ፣ አሁንም አላመኑበትም፤

38. ይኸውም ነቢዩ ኢሳይያስ፣“ጌታ ሆይ፤ ምስክርነታችንን ማን አመነ?የጌታ ክንድስ ለማን ተገለጠ?” ያለው ቃል እንዲፈጸም ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 12