ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ያዕቆብ 2:8-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. በመጽሐፍ፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” ተብሎ የተጻፈውን ክቡር ሕግ ብትፈጽሙ መልካም እያደረጋችሁ ነው።

9. አድልዎ ብታደርጉ ግን ኀጢአት መሥራታችሁ ነው፤ በሕግም ፊት እንደ ሕግ ተላላፊዎች ትቈጠራላችሁ፤

10. ምክንያቱም ሕግን ሁሉ የሚፈጽም ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ቢኖር፣ ሁሉን እንደ ተላለፈ ይቈጠራል።

11. “አታመንዝር” ያለ እርሱ ራሱ “አትግደልም” ብሎአልና። ባታመነዝር፣ ነገር ግን ብትገድል፣ ሕግ ተላላፊ ሆነሃል።

12. ስትናገሩም ሆነ ስታደርጉ ነጻነት በሚሰጠው ሕግ እንደሚፈረድባቸው ሰዎች ሁኑ፤

13. ምክንያቱም ምሕረት ያላደረገ ሁሉ ያለ ምሕረት ይፈረድበታል፤ ምሕረት በፍርድ ላይ ያይላል።

14. ወንድሞቼ ሆይ፤ አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ሥራ ግን ባይኖረውምን ይጠቅመዋል? እንዲህ ያለው እምነት ሊያድነው ይችላልን?

15. አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት የሚለብሱት ልብስም ሆነ የሚመገቡት ምግብ አጥተው፣

16. ከእናንተ መካከል አንዱ፣ “በሰላም ሂዱ፤ አይብረዳችሁ፤ ጥገቡ” ቢላቸው፣ ለሰውነታቸው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባይሰጣቸው፣ ምን ይጠቅማቸዋል?

17. እንዲሁ ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው።

18. ነገር ግን አንድ ሰው “አንተ እምነት አለህ፤ እኔ ሥራ አለኝ” ይላል።እምነትህን ከሥራ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ።

19. አንድ እግዚአብሔር እንዳለ ታምናለህ፤ መልካም ነው፤ አጋንንትም ይህንኑ ያምናሉ፤ በፍርሀትም ይንቀጠቀጣሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ያዕቆብ 2