ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕብራውያን 9:11-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ክርስቶስ አሁን ስላሉት መልካም ነገሮች ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ በሰው እጅ ወዳልተሠራችው፣ ከዚህ ፍጥረት ወዳ ልሆነችው ታላቅና ፍጹም ድንኳን ገባ።

12. የገባውም የፍየልንና የጥጃዎችን ደም ይዞ አይደለም፤ ነገር ግን የዘላለም ቤዛነት ሊያስገኝ የራሱን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ።

13. የውጭ አካላቸው ይነጻ ዘንድ በረከሱ ሰዎች ላይ የሚረጨው የፍየሎችና የኮርማዎች ደም እንዲሁም የፍየሎችና የጊደር ዐመድ የሚቀድሳቸው ከሆነ፣

14. በዘላለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር አልባ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እንድናመልክ ኅሊናችንን ከምውት ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን!

15. ስለዚህም የተጠሩት፣ ተስፋ የተሰጠውን የዘላለም ርስት እንዲቀበሉ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው፤ በመጀመሪያው ኪዳን ሥር በነበሩበት ጊዜ ከሠሩት ኀጢአት ነጻ ለማውጣት ቤዛ ሆኖ ሞቶአልና።

16. ኑዛዜ በሚኖርበት ጊዜ የተናዛዡን ሞት ማረጋገጥ ግድ ነው፤

17. ምክንያቱም ኑዛዜው የሚጸናው ሰውዬው ሲሞት ብቻ ነው፤ ነገር ግን ተናዛዡ በሕይወት እስካለ ድረስ ኑዛዜው ዋጋ አይኖረውም።

18. ስለዚህ የመጀመሪያው ኪዳን እንኳ ያለ ደም የጸና አልነበረም።

19. ሙሴ እያንዳንዱን የሕግ ትእዛዝ ለሕዝቡ ሁሉ ከተናገረ በኋላ የጥጆችን ደም ከውሃ፣ ከቀይ የበግ ጠጒርና ከሂሶጵ ጋር ወስዶ፣ በመጽሐፉና በሕዝቡ ላይ ረጨው፤

20. እንዲህም አለ፤ “እንድትጠብቁት እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የኪዳኑ ደም ይህ ነው።”

21. እንዲሁም ድንኳኒቱንና ማገልገያ ዕቃውን ሁሉ በደም ረጨው።

22. በርግጥ ከጥቂት ነገሮች በስተቀር ሁሉም ነገር በደም መንጻት እንዳለበት ሕጉ ያዛል፤ ደም ሳይፈስ ስርየት የለምና።

23. እንግዲህ የሰማያዊው ነገሮች ምሳሌ የሆኑት በእነዚህ ነገሮች ሊነጹ ግድ ነበር፤ በሰማይ ያሉት ነገሮች ግን ከዚህ በሚበልጥ መሥዋዕት ይነጻሉ።

24. ክርስቶስ የእውነተኛዪቱ ድንኳን ምሳሌ ወደ ሆነችውና በሰው እጅ ወደ ተሠራችው መቅደስ አልገባም፤ ነገር ግን አሁን ስለ እኛ በእግዚአብሔር ፊት ለመታየት፣ ወደ እርሷ ወደ ሰማይ ገባ።

25. ሊቀ ካህናት የራሱ ያልሆነውን ደም ይዞ በየዓመቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን እንደሚገባ፣ ክርስቶስ ራሱን ብዙ ጊዜ መሥዋዕት ለማድረግ ወደ ሰማይ አልገባም።

26. እንዲህ ቢሆን ኖሮ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ መከራን መቀበል ባስፈለገው ነበር። አሁን ግን በዘመናት መጨረሻ ራሱን መሥዋዕት በማድረግ ኀጢአትን ለማስወገድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተገልጦአል።

27. ሰው አንድ ጊዜ ሊሞት ከዚያም በኋላ በፍርድ ፊት ሊቆም ተወስኖበታል።

28. ክርስቶስ የብዙ ሰዎችን ኀጢአት ለመሸከም፣ እንዲሁ አንድ ጊዜ መሥዋዕት ሆኖአል፤ ሁለተኛ ጊዜም ይገለጣል፤ ይህም ለሚጠባበቁት ድነትን ለማምጣት እንጂ ኀጢአትን ለመሸከም አይደለም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕብራውያን 9