ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ቲቶ 3:4-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ነገር ግን የአዳኛችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ፍቅር በተገለጠ ጊዜ፣

5. ስላደረግነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን፣ ከምሕረቱ የተነሣ አዳነን። ያዳነንም ዳግም ልደት በሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ ነው፤

6. ይህንም መንፈስ እግዚአብሔር በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእኛ ላይ አትረፍርፎ አፈሰሰው፤

7. ይኸውም በጸጋው ጸድቀን የዘላለምን ሕይወት ተስፋ ይዘን ወራሾች እንድንሆን ነው።

8. ይህም የታመነ ቃል ነው። በእግዚአብሔር ያመኑቱ መልካሙን ነገር ለማድረግ ራሳቸውን አሳልፈው ይሰጡ ዘንድ እነዚህን ነገሮች አስረግጠህ እንድትናገር እፈልጋለሁ። ይህ መልካምና ለማንኛውም ሰው የሚጠቅም ነው።

9. ነገር ግን ከንቱ ከሆነ ክርክርና ከትውልድ ሐረግ ቈጠራ፣ ከጭቅጭቅና ስለ ሕግ ከሚነሣ ጠብ ራቅ፤ ይህ ዋጋ ቢስና ከንቱ ነውና።

10. መከፋፈል የሚያመጣን ሰው አንድ ጊዜ ምከረው፤ ለሁለተኛ ጊዜ አስጠንቅቀው፤ ከዚያ ካለፈ ከእርሱ ጋር አንዳች ነገር አይኑርህ።

11. እንዲህ ዐይነቱ ሰው የሳተና ኀጢአተኛ ነው፤ ራሱንም እንደሚኰንን ዕወቅ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ቲቶ 3