ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ቈላስይስ 1:24-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

24. ስለ እናንተ በተቀበልሁት መከራ አሁንም ደስ ይለኛል፤ ክርስቶስ ስለ አካሉ ስለ ቤተ ክርስቲያን ከተቀበለው መከራ የጐደለውን በሥጋዬ አሟላለሁ።

25. የእግዚአብሔርን ቃል በሙላት እንዳቀርብላችሁ ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ዐደራ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆኛለሁ፤

26. ይህም ቃል ከዘመናትና ከትውልዶች ተሰውሮ ምስጢር ሆኖ ቈይቶ ነበር፤ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል።

27. ለእነርሱም እግዚአብሔር የዚህ ምስጢር ክብር ባለጠግነት በአሕዛብ መካከል ምን ያህል እንደሆነ ለማሳወቅ መረጠ፤ እርሱም የክብር ተስፋ የሆነው በእናንተ ውስጥ ያለው ክርስቶስ ነው።

28. እኛም እያንዳንዱን ሰው በክርስቶስ ፍጹም አድርገን ማቅረብ እንችል ዘንድ፣ ሰውን ሁሉ በጥበብ ሁሉ እየመከርንና እያስተማርን እርሱን እንሰብካለን፤

29. እኔም በብርታት በውስጤ በሚሠራው በእርሱ ኀይል ሁሉ እየታገልሁ ለዚህ ዐላማ እጥራለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ቈላስይስ 1