ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 9:19-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. ከእናንተ አንዱ፣ “ታዲያ እንደዚህ ከሆነ እግዚአብሔር እስከ አሁን ለምን ይወቅሰናል? ምክንያቱም ፈቃዱን ሊቋቋም የሚችል ማን አለ?” ይለኝ ይሆናል።

20. ነገር ግን ለእግዚአብሔር መልስ የምትሰጥ አንተ ማን ነህ? “ሥራ ሠሪውን፣ ‘ለምን እንዲህ ሠራኸኝ?’ ይለዋልን?”

21. ሸክላ ሠሪ፣ ከሚሠራው ጭቃ፣ አንዳንዱን ሸክላ ለክብር፣ ሌላውን ደግሞ ለተራ አገልግሎት የማድረግ መብት የለውምን?

22. እግዚአብሔር ቊጣውን ለማሳየት፣ ኀይሉንም ለማሳወቅ ፈልጎ የቍጣው መግለጫ የሆኑትን፣ ለጥፋትም የተዘጋጁትን እጅግ ታግሦ ቢሆንሳ!

23. አስቀድሞ ለክብር ላዘጋጃቸው፣ የምሕረቱም መግለጫዎች ለሆኑት፣ የክብሩ ባለጠግነት እንዲታወቅ ይህን አድርጎ እንደሆነስ?

24. የጠራው ከአይሁድ ወገን ብቻ ሳይሆን ከአሕዛብ ወገን የሆነውን እኛን እንኳ ሳይቀር አይደለምን?

25. በሆሴዕ እንዲህ እንደሚል፤“ሕዝቤ ያልሆኑትን፣ ‘ሕዝቤ’ ብዬ እጠራቸዋለሁ”፤ያልተወደደችውንም ‘የተወደደችው’ ብዬ እጠራለሁ።

26. ደግሞም፣ “ ‘ሕዝቤ አይደላችሁም’፤ተብሎ በተነገራቸው በዚያ ቦታ፣‘የሕያው እግዚአብሔር ልጆች’ ተብለውይጠራሉ።”

27. ኢሳይያስም ስለ እስራኤል እንዲህ ሲል ይጮኻል፤“የእስራኤል ልጆች ቊጥር በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ቢሆንም፣ትሩፉ ብቻ ይድናል።

28. ጌታ ፍርዱን በምድር ላይ፣በፍጥነትና ለመጨረሻ ጊዜ ይፈጽማልና።”

29. ይኸውም ቀደም ሲል ኢሳይያስእንደ ተናገረው ነው፤“የሰራዊት ጌታ፣ ዘር ባያስቀርልን ኖሮ፣እንደ ሰዶም በሆን ነበር፤ገሞራንም በመሰልን ነበር።”

30. እንግዲህ ምን እንበል? በእምነት የሆነውን ጽድቅ፣ ለጽድቅ ያልደከሙት አሕዛብ አገኙት፤

31. ነገር ግን የጽድቅን ሕግ የተከታተሉት እስራኤል አላገኙትም።

32. ይህ ለምን ሆነ? በእምነት ሳይሆን በሥራ እንደሆነ አድርገው በመቊጠር ስለ ተከታተሉት ነው፤ እነርሱም፣ “በማሰናከያው ድንጋይ” ተሰናከሉ።

33. ይህም፣“እነሆ፤ ሰዎችን እንዲደናቀፉ የሚያደርግ ድንጋይ፣እንዲወድቁ የሚያደርግ ዐለት፣በጽዮን ላይ አስቀምጣለሁ፤ በእርሱም የሚያምን አያፍርም”ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሮሜ 9