ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 4:15-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ሕግ ቊጣን ያስከትላል፤ ሕግ በሌለበት ግን መተላለፍ አይኖርም።

16. ስለዚህ ተስፋው በእምነት መጥቶአል፤ ይኸውም ተስፋው በጸጋ እንዲሆንና ለአብርሃም ዘር ሁሉ ዋስትና ይሆን ዘንድ ነው፤ ይህም በሕግ የእርሱ ለሆኑት ብቻ ሳይሆን፣ በእምነት የአብርሃም ለሆኑትም ነው፤ እርሱም የሁላችን አባት ነው፤

17. ይህም “የብዙ ሕዝብ አባት አድርጌሃለሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው፤ እርሱም ለሙታን ሕይወትን በሚሰጥ፣ ያልነበረውንም እንደ ነበረ በሚያደርግ፣ ባመነበት አምላክ ፊት አባታችን ነው።

18. “ዘርህም እንዲሁ ይሆናል” ተብሎ ለእርሱ በተነገረው መሠረት፣ ምንም ተስፋ በሌለበት፣ አብርሃም በተስፋ አምኖ የብዙ ሕዝብ አባት ሆነ።

19. እርሱ የመቶ ዓመት ሰው ሆኖ ሳለ፣ የራሱም ሰውነት ሆነ የሣራ ማሕፀን ምዉት እንደ ነበረ እያወቀ በእምነቱ አልደከመም።

20. ይልቁንም በእምነቱ በመጽናት ለእግዚአብሔር ክብርን ሰጠ እንጂ፣ የእግዚአብሔርን ተስፋ አልተጠራጠረም፤

21. እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም በሙሉ ልብ ርግጠኛ ነበር።

22. ስለዚህ፣ “ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት።”

23. “ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት” የሚለው ቃል የተጻፈው ለእርሱ ብቻ አይደለም፤

24. ነገር ግን እግዚአብሔር ጽድቅ አድርጎ ለሚቈጥርልን፣ ጌታችን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው በእርሱ ለምናምን ለእኛም ጭምር ነው።

25. እርሱ ስለ ኀጢአታችን እንዲሞት ዐልፎ ተሰጠ፤ እኛን ጻድቅ አድርጎ ለማቅረብም ከሞት ተነሣ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሮሜ 4