ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 14:11-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤“ ‘እኔ ሕያው ነኝና’፤‘ጒልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር ይመሰክራል’ ” ይላል ጌታ።

12. ስለዚህ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን።

13. ስለዚህ እርስ በርሳችን፣ አንዱ በሌላው ላይ ከመፍረድ እንቈጠብ፤ በዚህ ፈንታ ግን በወንድምህ መንገድ ላይ የማሰናከያ ድንጋይ ወይም ወጥመድ እንዳታስቀምጥ ቊርጥ ሐሳብ አድርግ።

14. በጌታ በኢየሱስ ሆኜ በራሱ ንጹሕ ያልሆነ ምንም ምግብ እንደሌለ ተረድቻለሁ፤ ነገር ግን አንድ ሰው አንድን ነገር ንጹሕ እንዳልሆነ የሚቈጥር ከሆነ፣ ያ ነገር ለእርሱ ንጹሕ አይደለም።

15. ወንድምህ በምትበላው ምግብ የሚያዝን ከሆነ፣ በፍቅር አልተመላለስህም፤ ክርስቶስ የሞተለትን ወንድምህን በመብልህ አታጥፋው።

16. መልካም ነው ብለህ የምታስበው ነገር ክፉ ተብሎ እንዲነቀፍ አታድርግ።

17. የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም፣ በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ሐሤት ነው እንጂ፣ የመብልና የመጠጥ ጒዳይ አይደለም፤

18. በዚህ ሁኔታ ክርስቶስን የሚያገለግል እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛልና፤ በሰውም ዘንድ የተመሰገነ ነው።

19. ስለዚህ ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችንም የምንተናነጽበትን ማንኛውንም ጥረት እናድርግ።

20. ለምግብ ስትል የእግዚአብሔርን ሥራ አታፍርስ። ሁሉ ንጹሕ ነው፤ ነገር ግን ለሌላው ሰው የመሰናከያ ምክንያት የሚሆነውን መብላት ስሕተት ነው።

21. ለወንድምህ መሰናከል ምክንያት የሚሆነውን ሥጋን አለመብላት፣ ወይንን አለ መጠጣት፣ ወይም አንዳች ነገርን አለማድረግ መልካም ነው።

22. እንግዲያስ ስለ እነዚህ ነገሮች ያለህ እምነት በአንተና በእግዚአብሔር መካከል የተጠበቀ ይሁን፤ ትክክል ነው ብሎ በተቀበለው ነገር ራሱን የማይኰንን የተባረከ ሰው ነው።

23. ነገር ግን የሚጠራጠር ሰው ቢበላ በእምነት ስላልሆነ፣ ተፈርዶበታል፤ በእምነት ያልተደረገ ሁሉ ኀጢአት ነውና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሮሜ 14