ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ራእይ 8:4-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳኑ ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ ወደ እግዚአብሔር ፊት ወጣ።

5. መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሠዊያውን እሳት ሞላበትና ወደ ምድር ወረወረው፤ ነጐድጓድ፣ ድምፅ፣ መብረቅና የምድር መናወጥ ሆነ።

6. ከዚያም ሰባቱን መለከት የያዙት ሰባቱ መላእክት ለመንፋት ተዘጋጁ።

7. የመጀመሪያው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ደም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ወደ ምድር ተጣለ፤ የምድር አንድ ሦስተኛ ተቃጠለ፤ የዛፎችም አንድ ሦስተኛ ተቃጠለ፤ የለመለመውም ሣር ሁሉ ተቃጠለ።

8. ሁለተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ትልቅ ተራራ የሚመስል ነገር በእሳት እየተቀጣጠለ ወደ ባሕር ተጣለ፤ የባሕሩ አንድ ሦስተኛ ወደ ደም ተለወጠ፤

9. በባሕሩም ውስጥ ከሚኖሩት ሕያዋን ፍጡራን አንድ ሦስተኛ ሞተ፤ የመርከቦችም አንድ ሦስተኛ ወደመ።

10. ሦስተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ እንደ ችቦ የሚነድ ታላቅ ኮከብ በወንዞች አንድ ሦስተኛና በውሃ ምንጮች ላይ ከሰማይ ወደቀ፤

11. የኮከቡም ስም “እሬቶ” ይባል ነበር። የውሃውም አንድ ሦስተኛ መራራ ሆነ፤ ውሃው መራራ ከመሆኑ የተነሣም ብዙ ሰዎች ሞቱ።

12. አራተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ የብርሃናቸው አንድ ሦስተኛ ይጨልም ዘንድ፣ የፀሓይ አንድ ሦስተኛ፣ የጨረቃም አንድ ሦስተኛ፣ የከዋክብትም አንድ ሦስተኛ ተመታ፤ የቀንም አንድ ሦስተኛ፣ የሌሊቱም አንድ ሦስተኛ ብርሃን አንዳይሰጥ ተከለከለ።

13. ከዚያም ተመለከትሁ፤ አንድ ንስር በሰማይ መካከል ይበር ነበር፤ በታላቅ ድምፅም፣ “የቀሩት ሦስቱ መላእክት መለከት ስለሚነፉ፣ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው! ወዮላቸው! ወዮላቸው!” ሲል ሰማሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ራእይ 8