ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ራእይ 6:8-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. እኔም ተመለከትሁ፤ እነሆ፤ ግራጫ ፈረስ ቆሞ አየሁ፤ ተቀምጦበት የነበረው ስሙ ሞት ነበር፤ ሲኦልም ከኋላ ይከተለው ነበር። እነርሱም በሰይፍ፣ በራብ፣ በመቅሠፍትና በምድር አራዊት እንዲገድሉ በምድር አንድ አራተኛ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።

9. አምስተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁትም ምስክርነት የታረዱትን ሰዎች ነፍሶች ከመሠዊያው በታች አየሁ።

10. እነርሱም በታላቅ ድምፅ፣ “ሁሉን የምትገዛ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፤ እስከ መቼ አትፈርድም? እስከ መቼስ ደማችንን በምድር በሚኖሩት ላይ አትበቀልም?” አሉ።

11. ከዚያም ለእያንዳንዳቸው ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤ ወደ ፊት እንደ እነርሱ የሚገደሉ የአገልጋይ ባልንጀሮቻቸውና ወንድሞቻቸው ቊጥር እስኪሞላ ድረስ ጥቂት ጊዜ እንዲታገሡ ተነገራቸው።

12. ስድስተኛውን ማኅተም ሲፈታ ተመለከትሁ፤ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ፀሓይም እንደ ማቅ ጠቈረች። ጨረቃም በሙሉ እንደ ደም ቀላች፤

13. የበለስ ዛፍ በብርቱ ነፋስ ስትወዛወዝ ያልበሰለው ፍሬ ከእርሷ እንደሚረግፍ፣ የሰማይ ከዋክብት ወደ ምድር ረገፉ።

14. ሰማይ እንደ ጥቅልል መጽሐፍ ተጠቅልሎ ዐለፈ፤ ተራሮችና ደሴቶችም ሁሉ ከስፍራቸው ተወገዱ።

15. ከዚህ በኋላ የምድር ነገሥታትና ገዦች፣ የጦር መኰንኖች፣ ሀብታሞች፣ ብርቱዎች፣ ባሮችና ጌቶች ሁሉ በዋሻዎችና በተራሮች ዐለት ውስጥ ተሸሸጉ፤

16. ተራሮቹንና ዐለቶቹንም፣ “በላያችን ውደቁ፤ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቊጣ ሰውሩን፤

17. ታላቁ የቊጣቸው ቀን መጥቶአልና፤ ማንስ ሊቆም ይችላል?” አሏቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ራእይ 6