ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ራእይ 22:13-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. አልፋና ዖሜጋ፣ ፊተኛውና ኋለኛው፣ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።

14. “ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስና በበሮቿም በኩል ወደ ከተማዪቱ ለመግባት መብት እንዲኖራቸው ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው።

15. ውሾች፣ አስማተኞች፣ ሴሰኞች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ ውሸትን የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ።

16. “እኔ ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች እንዲመሰክር መልአኬን ለአብያተ ክርስቲያናት ልኬአለሁ። እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፣ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ።”

17. መንፈስና ሙሽራዪቱ፣ “ና” ይላሉ፤ የሚሰማም፣ “ና” ይበል፤ የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግም ሁሉ የሕይወትን ውሃ በነጻ ይውሰድ።

18. የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል የሚሰማውን ሁሉ አስጠነቅቃለሁ፤ ማንም በዚህ ቃል ላይ አንዳች ቢጨምር፣ እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ይጨምርበታል፤

19. ማንም በዚህ የትንቢት መጽሐፍ ከተጻፈው ቃል አንዳች ቢያጐድል፣ እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ ዕድሉን ያጐድልበታል።

20. እነዚህን ነገሮች የሚመሰክረው፣ “አዎ፣ ቶሎ እመጣለሁ” ይላል።አሜን፤ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ራእይ 22