ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ራእይ 19:7-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. የበጉ ሰርግ ስለ ደረሰ፣የእርሱም ሙሽራ ራሷን ስላዘጋጀች፣ደስ ይበለን፤ ሐሤት እናድርግክብርም እንስጠው።

8. የሚያንጸባርቅና ንጹሕ፣ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ እንድትለብስ ተሰጣት።”ከተልባ እግር የተሠራው ቀጭን ልብስ የቅዱሳን የጽድቅ ሥራ ነው።

9. መልአኩም፣ “ ‘ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው’ ብለህ ጻፍ” አለኝ፤ ቀጥሎም፣ “እነዚህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃሎች ናቸው” አለኝ።

10. እኔም ልሰግድለት በእግሩ ሥር ተደፋሁ፤ እርሱ ግን፣ “ተው! ይህን አታድርግ! እኔም ከአንተና የኢየሱስን ምስክር ከያዙት ወንድሞችህ ጋር አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና” አለኝ።

11. ከዚያም ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆ አንድ ነጭ ፈረስ ነበረ፤ በፈረሱም ላይ፣ “ታማኝና እውነተኛ” የሚባል ተቀምጦ ነበር፤ እርሱም በጽድቅ ይፈርዳል፤ ይዋጋልም።

12. ዐይኖቹ እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፤ በራሱም ላይ ብዙ ዘውዶች አሉ። ከእርሱ በቀር ማንም የማያውቀው ስም በእርሱ ላይ ተጽፎአል።

13. እርሱ በደም የተነከረ ልብስ ለብሶአል፤ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ነው።

14. የሰማይም ሰራዊት ነጭ፣ ንጹሕና ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ ለብሰው፣ በነጫጭ ፈረሶች ላይ ተቀምጠው ይከተሉት ነበር።

15. ሕዝቦችን የሚመታበት ስለታም ሰይፍ ከአፉ ወጣ፤ “በብረት በትርም ይገዛቸዋል።” እርሱም ሁሉን ቻይ የሆነውን የእግዚአብሔርን የብርቱ ቍጣ ወይን መጭመቂያ ይረግጣል።

16. በልብሱና በጭኑ ላይ እንዲህ የሚል ስም ተጽፎአል፤“የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ።”

17. ቀጥሎም አንድ መልአክ በፀሓይ ውስጥ ቆሞ አየሁ፤ እርሱም በሰማይ መካከል ለሚበሩ ወፎች ሁሉ እንዲህ ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ “ኑ፤ ወደ ታላቁ የእግዚአብሔር እራት ተሰብሰቡ፤

18. የምትሰበሰቡትም የነገሥታትን ሥጋ፣ የጦር አዛዦችን ሥጋ፣ የብርቱ ሰዎችን ሥጋ፣ የፈረሶችንና የፈረሰኞችን ሥጋ እንዲሁም የሰዎችን ሁሉ፣ ይኸውም የጌቶችንና የባሮችን፣ የታናናሾችንና የታላላቆችን ሥጋ እንድትበሉ ነው።”

19. ከዚህ በኋላ አውሬው፣ የምድር ነገሥታትና ሰራዊታቸው በፈረሱ ላይ ከተቀመጠውና ከሰራዊቱ ጋር ለመዋጋት ተሰብስበው አየሁ።

20. ነገር ግን አውሬው ተያዘ፤ ከእርሱም ጋር በፊቱ ምልክቶችን ያደርግ የነበረው ሐሰተኛው ነቢይ ተያዘ። በእነዚህ ምልክቶች የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትንና ለምስሉ የሰገዱትን አሳተ። ሁለቱም በሕይወት እንዳሉ በዲን ወደሚቃጠለው የእሳት ባሕር ተጣሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ራእይ 19