ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ራእይ 18:10-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ሥቃይዋንም በመፍራት በሩቅ ቆመው እንዲህ ይላሉ፤“አንቺ ታላቂቱ ከተማ ወዮልሽ! ወዮልሽ!”አንቺ ባቢሎን ብርቱዪቱ ከተማ፣ፍርድሽ በአንድ ሰዓት ውስጥ መጥቶአል።”

11. “ጭነታቸውን ከእንግዲህ የሚገዛ ስለሌለ፣ የምድር ነጋዴዎችም ስለ እርሷ ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉ፤

12. ጭነቱም፦ ወርቅ፣ ብር፣ የከበረ ድንጋይ፣ ዕንቍ፣ ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ፣ ሐምራዊ ልብስ፣ ሐር ልብስ፣ ቀይ ልብስ፣ መልካም ሽታ ያለው ዕንጨት ሁሉ፣ ከዝሆን ጥርስ፣ ከውድ ዕንጨት፣ ከናስ፣ ከብረትና ከእብነ በረድ የተሠራ ዕቃ ሁሉ፣

13. ቀረፋ፣ ቅመም፣ ከርቤ፣ ቅባት፣ ዕጣን፣ የወይን ጠጅ፣ የወይራ ዘይት፣ የተሰለቀ ዱቄት፣ ስንዴ፣ ከብቶች፣ በጎች፣ ፈረሶች፣ ሠረገሎች፣ እንዲሁም ባሮችና የሰዎች ነፍሶች ነው።

14. እነርሱም፣ ‘የተመኘሽው ፍሬ ከአንቺ ርቆአል፤ ብልጽግናሽና ክብርሽ ሁሉ ጠፍቶአል፤ ዳግመኛም ተመልሶ አይመጣም” ይላሉ።

15. እነዚህን ነገሮች በመሸጥ በእርሷ የበለጸጉ ነጋዴዎች ሥቃይዋን ፈርተው በሩቅ ይቆማሉ፤ እነርሱም ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉም፤

16. ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲህ ይላሉ፤“ቀጭን የተልባ እግር፣ ሐምራዊና ቀይ ልብስ የለበሰች፣በወርቅ፣ በከበረ ድንጋይና በዕንቍም ያጌጠች፣ታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት!

17. ያ ሁሉ ሀብት በአንድ ሰዓት ውስጥ ጠፋ።”“የመርከብ አዛዦች ሁሉ፣ በመርከብ የሚጓዙ መንገደኞች ሁሉ፣ የመርከብ ሠራተኞችና ኑሮአቸውን በባሕር ላይ የመሠረቱ ሁሉ በሩቅ ይቆማሉ።

18. እርሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ፣ ‘እንደዚች ያለ ታላቅ ከተማ ከቶ የት አለ?’ እያሉ ይጮኻሉ።

19. በራሳቸውም ላይ አቧራ ነስንሰው እያለ ቀሱና እያዘኑ እንዲህ ብለው ጮኹ፤“ ‘በባሕር ላይ መርከቦች ያላቸው ሁሉ፣በእርሷም ሀብት የበለጸጉ፣ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት!በአንድ ሰዓት ውስጥ ጠፍታለች።

20. ሰማይ ሆይ፤ በእርሷ ላይ ሐሤትአድርግ፤ቅዱሳን፣ ሐዋርያትና ነቢያትም ሐሤት አድርጉ፤በእናንተ ላይ ባደረሰችው ነገርእግዚአብሔር ፈርዶባታልና።’ ”

21. ከዚያም አንድ ብርቱ መልአክ፣ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ የሚመስል ድንጋይ አንሥቶ ወደ ባሕር ወረወረው፤ እንዲህም አለ፤“ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን፣እንዲህ ባለ ኀይል ትወረወራለች፤ተመልሳም አትገኝም።

22. የበገና ደርዳሪዎችና የሙዚቀኞች ድምፅ፣የዋሽንትና የመለከት ነፊዎች ድምፅ፣ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይሰማም፤የእጅ ጥበብ ባለ ሙያ፣ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይገኝም፤የወፍጮ ድምፅም፣ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይሰማም።

23. የመብራት ብርሃን፣ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይበራም፤የሙሽራውና የሙሽራዪቱ ድምፅ፣ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይሰማም፤ነጋዴዎችሽ የዓለም ታላላቅ ሰዎች ነበሩ፤በአስማትሽም ሕዝቦች ሁሉ ስተዋል።

24. በእርሷም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን፣በምድርም የተገደሉት ሁሉ ደም ተገኘ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ራእይ 18