ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ራእይ 1:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ቶሎ መሆን የሚገባውን ነገር ለአገልጋዮቹ እንዲያሳይ፣ እግዚአብሔር ለእርሱ የሰጠው የኢየሱስ ክርስቶስ ራእይ ይህ ነው፤ ኢየሱስም መልአኩን ልኮ ለአገልጋዩ ለዮሐንስ ገለጠለት፤

2. እርሱም ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት ያየውን ሁሉ መሰከረ።

3. ዘመኑ ቀርቦአል፤ እንግዲህ ይህን የትንቢት ቃል የሚያነብ ብፁዕ ነው፤ የሚሰሙትና የተጻፈውንም የሚጠብቁ ብፁዓን ናቸው።

4. ከዮሐንስ፤በእስያ አውራጃ ለሚገኙ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት፤ካለው፣ ከነበረውና ከሚመጣው፣ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት፣

5. እንዲሁም ታማኝ ምስክር፣ ከሙታን በኵርና የምድር ነገሥታት ገዥ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።ለወደደንና ከኀጢአታችንም በደሙ ነጻ ላወጣን፣

6. አምላኩንና አባቱን እንድናገለግልም መንግሥትና ካህናት ላደረገን፣ ለእርሱ ክብርና ኀይል ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁ አሜን።

7. እነሆ፤ በደመና ይመጣል፤የወጉት እንኳ ሳይቀሩ፣ዐይን ሁሉ ያየዋል፤የምድርም ሕዝቦች ሁሉ ከእርሱ የተነሣ ዋይ ዋይ ይላሉ።አዎ! ይህ ሁሉ ይሆናል፤ አሜን።

8. “ያለውና የነበረው፣ የሚመጣውም፣ ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ፣ አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ” ይላል።

9. እኔ ወንድማችሁ ዮሐንስ፣ ከእናንተ ጋር አብሬ በኢየሱስ መከራውንና መንግሥቱን፣ ትዕግሥቱንም ተካፋይ የሆንሁ፣ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክርነት ፍጥሞ በምትባል ደሴት ነበርሁ።

10. በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፤ የመለከትን ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ ከበስተ ኋላዬ ሰማሁ፤

11. ድምፁም፣ “የምታየውን በጥቅልል መጽሐፍ ጽፈህ በኤፌሶን፣ በሰምርኔስ፣ በጴርጋሞን፣ በትያጥሮን፣ በሰርዴስ፣ በፊላድልፍያና በሎዶቅያ ወደሚገኙት ወደ ሰባቱ የእስያ አብያተ ክርስቲያናት ላክ” አለ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ራእይ 1