ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 6:11-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን።

12. እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በለን።

13. ወደ ፈተናም አታግባን ከክፉው አድነን እንጂ፣ መንግሥት፣ ኃይል፣ ክብርም፣ ለዘለዓለሙ ያንተ ነውና፤ አሜን። ’

14. እናንተ የበደሏችሁን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ እናንተን ይቅር ይላችኋል።

15. ነገር ግን የሰዎችን ኀጢአት ይቅር የማትሉ ከሆነ፣ አባታችሁም ኀጢአታችሁን ይቅር አይልላችሁም።

16. “ስትጾሙ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ እነርሱ መጾማቸው እንዲታወቅላቸው ሆን ብለው በፊታቸው ላይ የሐዘን ምልክት ያሳያሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ እንዲህ የሚያደርጉ ዋጋቸውን በሙሉ ተቀብለዋል።

17. አንተ ግን በምትጾምበት ጊዜ ፊትህን ታጠብ፤ ራስህንም ተቀባ፤

18. በዚህም መጾምህ በስውር ያለው አባትህ ብቻ የሚያውቀው፣ ከሰዎች ግን የተሰወረ ይሆናል፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል።

19. “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በሚችልበት በዚህ ምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ።

20. ነገር ግን ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በማይችልበት በዚያ በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ፤

21. ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያው ይሆናልና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 6