ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 5:14-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትደበቅ አትችልም፤

15. ሰዎችም መብራት አብርተው ከዕንቅብ ሥር አያስቀምጡትም፤ በቤት ውስጥ ላሉት ሁሉ እንዲያበራ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጡታል እንጂ።

16. እንደዚሁም ሰዎች መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ።

17. “ሕግንና የነቢያትን ቃል ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ለመፈጸም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም።

18. እውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ሕግ ሁሉ ይፈጸማል እንጂ ከሕግ አንዲት ፊደል ወይም አንዲት ነጥብ እንኳ አትሻርም።

19. ስለዚህ ማንም ከእነዚህ ትእዛዛት አነስተኛዪቱን እንኳን ቢተላለፍ፣ ሌሎችንም እንዲተላለፉ ቢያስተምር በመንግሥተ ሰማይ ታናሽ ተብሎ ይጠራል፤ ነገር ግን እነዚህን ትእዛዛት እየፈጸመ ሌሎችም እንዲፈጽሙ የሚያስተምር በመንግሥተ ሰማይ ታላቅ ይባላል።

20. ጽድቃችሁ ከፈሪሳውያንና ከኦሪት ሕግ መምህራን ጽድቅ ልቆ ካልተገኘ መንግሥተ ሰማይ መግባት አትችሉም።

21. “ለቀደሙት ሰዎች፣ ‘አትግደል፤ የገደለ ይፈረድበታል’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤

22. እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወንድሙን ያለ አግባብ የሚቈጣ ይፈረድበታል፤ ማንም ወንድሙን ‘ጅል’ የሚል በሸንጎ ፊት ይጠየቅበታል፤ ‘ደደብ’ የሚለው ደግሞ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይጠብቀዋል።

23. “ስለዚህ መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በምታቀርብበት ጊዜ ወንድምህ የተቀየመብህ ነገር መኖሩ ትዝ ቢልህ፣

24. መባህን በዚያው በመሠዊያው ፊት ተወው፤ በመጀመሪያ ሄደህ ከወንድምህ ጋር ተስማማ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን ለእግዚአብሔር አቅርብ።

25. “የከሰሰህ ባላጋራህ እንዳያስፈርድብህ፣ ዳኛውም ለአሳሪ አሳልፎ እንዳይሰጥህ፣ በወህኒም እንዳትጣል፣ በመንገድ ላይ ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ።

26. እውነት እልሃለሁ፤ ካስፈረደብህ ግን የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ አትወጣም።

27. “ ‘አታመንዝር’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 5