ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 27:12-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ሲከሱት ግን ምንም መልስ አልሰጠም።

13. በዚህ ጊዜ ጲላጦስ፣ “ስንት ነገር አቅርበው እንደሚከሱህ አትሰማምን?” አለው።

14. እርሱ ግን አገረ ገዥው እስኪገረም ድረስ ለቀረበበት ክስ አንዲት ቃል እንኳ አልመለሰም።

15. አገረ ገዥው ሕዝቡ በበዓሉ እንዲፈታላቸው የሚጠይቁትን አንድ እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው።

16. በዚያን ጊዜ በዐመፅ የታወቀ በርባን የሚባል እስረኛ ነበር።

17. ሕዝቡ እንደተሰበሰቡ ጲላጦስ፣ “ከበርባንና ክርስቶስ ከሚባለው ከኢየሱስ፣ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው፤

18. ጲላጦስም በቅናት አሳልፈው እንደሰጡት ያውቅ ነበርና።

19. በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ፣ “በእርሱ ምክንያት ዛሬ በሕልም ብዙ ስለተሠቃየሁ፣ በዚያ ንጹሕ ሰው ላይ ምንም ነገር እንዳታደርግ” የሚል መልእክት ላከችበት።

20. ነገር ግን የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች በርባን እንዲፈታላቸው ኢየሱስ ግን እንዲገደል ይለምኑ ዘንድ ሕዝቡን ያግባቡ ነበር።

21. አገረ ገዥውም፣ “ከሁለቱ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” በማለት ጠየቀ።እነርሱም፤ “በርባንን!” በማለት መለሱ።

22. ጲላጦስም፣ “ታዲያ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስንስ ምን ላድርገው?” አላቸው።ሁሉም፣ “ይሰቀል!” አሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 27