ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 26:36-49 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

36. ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄደ፤ እነርሱንም፣ “ወደዚያ ሄጄ በምጸልይበት ጊዜ እናንተ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው።

37. ከእርሱም ጋር ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስ ልጆች ይዞ ሄዶ ይተክዝና ይጨነቅ ጀመር፤

38. ከዚያም፣ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝናለች፤ ከእኔ ጋር በመትጋት እዚሁ ቈዩ” አላቸው።

39. ጥቂት ዕልፍ ብሎ በግንባሩ በመደፋት፣ “አባቴ ሆይ፤ ቢቻል ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ፤ ነገር ግን እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን አንተ እንደምትፈልገው ይሁን” ብሎ ጸለየ።

40. ከዚያም ተመልሶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሲመጣ፣ ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ፤ ከእኔ ጋር ለአንድ ሰዓት እንኳ መትጋት አቃታችሁን?

41. ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጕና ጸልዩ፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።”

42. እንደ ገና ለሁለተኛ ጊዜ ሄዶ፣ “አባት ሆይ፤ ይህ ሳልጠጣው የማያልፍ ጽዋ ከሆነ፣ ፈቃድህ ይፈጸም” ብሎ ጸለየ።

43. እንደ ገናም በመጣ ጊዜ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ስለ ነበር ተኝተው አገኛቸው።

44. ትቶአቸውም እንደ ገና በመሄድ ለሦስተኛ ጊዜ ቀደም ብሎ የጸለየውን ጸሎት ደገመ።

45. ከዚያም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም ዐርፋችሁ ተኝታችኋል? እነሆ፣ ሰዓቱ ቀርቦአል፤ የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ ዐልፎ ይሰጣል፤

46. ተነሡ እንሂድ፤ አሳልፎ የሚሰጠኝም እየመጣ ነው።”

47. በመናገር ላይ እያለ፣ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ዘንድ የተላኩ ሰይፍና ዱላ የያዙ ብዙ ሰዎችም አብረውት ነበሩ።

48. ይሁዳም፣ “እኔ የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት” ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ስለ ነበር፣

49. በቀጥታ ወደ ኢየሱስ ሄዶ፣ “መምህር ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን” በማለት ሳመው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 26