ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 25:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማይ መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ ዐሥር ልጃገረዶችን ትመስላለች።

2. ከእነርሱም አምስቱ ልጃገረዶች ዝንጉዎች፣ አምስቱ ደግሞ አስተዋዮች ነበሩ፤

3. ዝንጉዎቹ መብራት ይዘው መጠባበቂያ ዘይት አልያዙም ነበር።

4. አስተዋዮቹ ግን ከመብራታቸው ጋር መጠባበቂያ ዘይት በማሰሮ ይዘው ነበር።

5. ሙሽራው በዘገየ ጊዜ፣ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ።

6. “እኩለ ሌሊት ላይ፣ ‘ሙሽራው እየመጣ ነው፤ ወጥታችሁ ተቀበሉት!’ የሚል ጥሪ ተሰማ።

7. “በዚህ ጊዜ ልጃገረዶቹ ሁሉ ተነሥተው መብራቶቻቸውን እየተረኰሱ መዘጋጀት ያዙ።

8. ዝንጉዎቹ አስተዋዮቹን፣ ‘መብራታችን ሊጠፋብን ስለ ሆነ፣ ከዘይታችሁ ስጡን’ አሏቸው።

9. “አስተዋዮቹ ልጃገረዶች ግን መልሰው፣ ‘ያለን ዘይት ለእኛም ለእናንተም ላይበቃ ስለሚችል፣ ሄዳችሁ ከሻጮች ለራሳችሁ ግዙ’ አሏቸው።

10. “ዘይት ሊገዙ እንደሄዱ፣ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩት ልጃገረዶችም ወደ ሰርጉ ግብዣ አብረውት ገቡ፤ በሩም ተዘጋ።

11. “ዘግየት ብለው ሌሎቹ ልጃገረዶች መጥተው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በሩን ክፈትልን’ አሉ።

12. “እርሱ ግን መልሶ፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ አላውቃችሁም’ አላቸው።

13. “እንግዲህ ቀኑን ወይም ሰዓቱን ስለማታውቁ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 25