ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 23:6-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. በግብዣ ቦታ የከበሬታ ስፍራ፣ በምኵራብም የመጀመሪያውን መቀመጫ መያዝ ይወዳሉ።

7. እንዲሁም በገበያ መካከል ሰላምታ መቀበልንና በሰዎች አንደበት ‘መምህር’ ተብለው መጠራትን ይሻሉ።

8. “እናንተ ግን ‘መምህር’ ተብላችሁ አትጠሩ፤ አስተማሪያችሁ አንድ ብቻ ነው፣ እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁና።

9. በሰማይ ያለ አንድ አባት ስላላችሁ፣ በምድር ማንንም ‘አባት’ ብላችሁ አትጥሩ።

10. መምህራችሁ አንዱ ክርስቶስ ስለ ሆነ፣ ‘መምህር’ ተብላችሁ አትጠሩ።

11. ከመካከላችሁ ከሁላችሁ የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል፤

12. ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ይዋረዳል፣ ራሱን የሚያዋርድ ግን ይከበራል።

13. “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማይ እንዳይገቡ በሰዎች ላይ በሩን ስለ ምትዘጉባቸው ወዮላችሁ! እናንተ ራሳችሁ አትገቡም፤ መግባት የሚፈልጉትንም አታስገቡም።

14. እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ የመበለቶችን ቤት እያራቈታችሁ፣ ለሰው ይምሰል ረዥም ጸሎት ስለምታደርጉ የከፋ ፍርድ ትቀበላላችሁ።

15. “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ አንድን ሰው ወደ አይሁድ ሃይማኖት ለማስገባት በባሕርና በየብስ ስለምትጓዙ፣ ባመነም ጊዜ ከእናንተ በእጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት ወዮላችሁ።

16. “እናንተ ዕውር መሪዎች፤ ወዮላችሁ! ‘ማንም በቤተ መቅደስ ቢምል ምንም አይደለም፤ ነገር ግን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ባለው ወርቅ ቢምል መሐላው ይደርስበታል’ ትላላችሁ።

17. እናንተ የታወራችሁ ተላላዎች! ከወርቁና ወርቁን ከቀደሰው ቤተ መቅደስ የቱ ይበልጣል?

18. እንዲሁም፣ ‘ማንም በመሠዊያው ቢምል ምንም አይደለም፤ ነገር ግን በላዩ ላይ ባለው መባ ቢምል መሐላው ይደርስበታል’ ትላላችሁ፤

19. እናንተ ዕውሮች፤ ከመባውና መባውን ከቀደሰው መሠዊያ የቱ ይበልጣል?

20. ስለዚህ፣ በመሠዊያው የማለ፣ በመሠዊያውና በላዩ ላይ ባለው ሁሉ ይምላል።

21. እንዲሁም በቤተ መቅደሱ የማለ፣ በቤተ መቅደሱና በውስጡ በሚያድረው ይምላል።

22. በሰማይ የማለም በእግዚአብሔር ዙፋንና በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ይምላል።

23. “እናንት ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! ከአዝሙድ፣ ከእንስላልና ከከሙን ዐሥራት እየሰጣችሁ በሕጉ ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን ማለትም ፍትሕን፣ ምሕረትንና ታማኝነትን ግን ንቃችኋልና፤ እነዚያን ሳትተዉ እነዚህን ማድረግ በተገባችሁ ነበር፤

24. እናንት የታወራችሁ መሪዎች፤ ትንኝን አጥርታችሁ ትጥላላችሁ፤ ግመልን ግን ትውጣላችሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 23