ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 20:10-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. በመጀመሪያ የተቀጠሩት ሲቀርቡ ብልጫ ያለው ክፍያ የሚያገኙ መስሎአቸው ነበር፤ ነገር ግን እነርሱም አንዳንድ ዲናር ተከፈላቸው።

11. ክፍያውን ሲቀበሉ በባለቤቱ ላይ በማጕረምረም፣

12. ‘እነዚህ በመጨረሻ የተቀጠሩት አንድ ሰዓት ብቻ ሲሠሩ፣ ቀኑን ሙሉ በሥራ ስንደክምና በፀሐይ ስንንቃቃ ከዋልነው ጋር እንዴት እኩል ትከፍለናለህ?’ አሉት።

13. “እርሱም አንደኛውን ሠራተኛ እንዲህ አለው፤ ‘ወዳጄ ሆይ፤ በደል አላደረስሁብህም፤ በአንድ ዲናር ለመሥራት ከእኔ ጋር ተስማምተህ አልነበረምን?

14. በል ድርሻህን ይዘህ ሂድ፤ ለአንተ የሰጠሁትን ያህል በመጨረሻ ለመጣውም ሰው መስጠት እፈልጋለሁ።

15. ታዲያ በራሴ ገንዘብ የፈለግሁትን ማድረግ አልችልምን? ወይስ ቸር በመሆኔ ምቀኝነት ያዘህን?’

16. “ስለዚህ ኋለኞች ፊተኞች፣ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ።”

17. ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ላይ ሳለ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ወስዶ እንዲህ አላቸው፤

18. “እንግዲህ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዳችን ነው፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለኦሪት ሕግ መምህራን አልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም እንዲሞት ይፈርዱበታል፤

19. እንዲያላግጡበት፣ እንዲገርፉትና እንዲሰቅሉት ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሞት ይነሣል።”

20. ከዚያም፣ የዘብዴዎስ ልጆች እናት ከልጆቿ ጋር ወደ ኢየሱስ ቀርባ በፊቱ ተንበርክካ እየሰገደች፣ አንድ ነገር እንዲያደርግላት ለመነችው።

21. እርሱም፣ “ምን ትፈልጊያለሽ?” አላት።እርሷም፣ “እነዚህ ሁለት ልጆቼ፣ በመንግሥትህ አንዱ በቀኝህ፣ አንዱ በግራህ እንዲቀመጡ ፍቀድ” አለችው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 20