ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 18:9-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. እንዲሁም ዐይንህ ለመሰናክል ምክንያት ቢሆንብህ፣ አውጥተህ ጣለው፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል፣ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል።

10. “ከእነዚህ ከታናናሾች መካከል አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ እላችኋለሁና፤ በሰማይ ያሉት መላእክታቸው በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ሁል ጊዜ ያያሉ፤

11. የሰው ልጅ የጠፉትን ለማዳን መጥቶአልና።

12. “እስቲ ንገሩኝ፤ አንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩትና ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋውን ለመፈለግ አይሄድምን?

13. እውነት እላችኋለሁ፣ የጠፋውን በግ ሲያገኝ፣ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በዚያ በተገኘው ደስ ይለዋል።

14. እንደዚሁም ከእነዚህ ከታናናሾቹ መካከል አንዱ እንኳ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም።

15. “ወንድምህ ቢበድልህ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻ ሆናችሁ ጥፋቱን ንገረው። ቢሰማህ፣ ወንድምህን እንደ ገና የራስህ ታደርገዋለህ።

16. ባይሰማህ ግን ቃል ሁሉ በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች ፊት ስለሚጸና፣ አንድ ወይም ሁለት ሰው ይዘህ አነጋግረው።

17. እነርሱን ባይሰማ ለቤተ ክርስቲያን ንገር፤ ቤተ ክርስቲያንንም ባይሰማ እንደ አሕዛብና እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ ቊጠረው።

18. “እውነት እላችኋለሁ፤ በምድር ያሰራችሁት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የፈታችሁት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።

19. “ደግሞም እውነት እላችኋለሁ፤ በምድር ላይ ሁለት ሆናችሁ ስለ ምንም ነገር በመስማማት ብትጠይቁ በሰማይ ያለው አባቴ ያደርግላችኋል፤

20. ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት መካከል በዚያ እገኛለሁና።”

21. በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “ጌታ ሆይ፤ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 18