ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 17:5-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. እርሱ እየተናገረ ሳለ፣ ብሩህ ደመና ሸፈናቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፣ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ ተሰማ።

6. ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲሰሙ ደንግጠው በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ።

7. ኢየሱስም ቀርቦ ነካቸውና፣ “ተነሡ፤ አትፍሩ” አላቸው።

8. ቀና ብለው ሲመለከቱም ከኢየሱስ በስተቀር ሌላ ማንንም አላዩም።

9. ከተራራው በመውረድ ላይ ሳሉ ኢየሱስ፣ “የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም እንዳትናገሩ” ብሎ አዘዛቸው።

10. ደቀ መዛሙርቱም፣ “ታዲያ የኦሪት ሕግ መምህራን፣ ኤልያስ አስቀድሞ መምጣት አለበት የሚሉት ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።

11. እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ኤልያስ በርግጥ መጥቶ ሁሉንም ነገር ያስተካክላል፤

12. ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ኤልያስ መጥቶአል፤ ሆኖም የፈለጉትን ነገር አደረጉበት እንጂ አላወቁትም። እንዲሁም የሰው ልጅ በእጃቸው መከራን ይቀበላል።”

13. በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የነገራቸው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን ተረዱ።

14. ወደ ሕዝቡ እንደ ተመለሱ፣ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ በፊቱ ተንበረከከና እንዲህ አለ፤

15. “ጌታ ሆይ፤ እባክህ ልጄን ማርልኝ፤ በሚጥል በሽታ እጅግ እየተሠቃየ ነው፤ ብዙ ጊዜ እሳት ውስጥ ይወድቃል፤ ውሃ ውስጥም ይገባል፤

16. ወደ ደቀ መዛሙርትህ አመጣሁት፤ ነገር ግን ሊፈውሱት አልቻሉም።”

17. ኢየሱስም፣ “አንት የማታምን ጠማማ ትውልድ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ፤ እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ። ልጁን ወደዚህ አምጡት” አለ።

18. ከዚያም ኢየሱስ ጋኔኑን ገሠጸውና ከልጁ ወጣ፤ ልጁም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነ።

19. ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “እኛ ጋኔኑን ማስወጣት ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።

20. እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እምነታችሁ በማነሱ ምክንያት ነው፤ እላችኋለሁ፤ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህንን ተራራ፣ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደዚያ ሂድ’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ነገር አይኖርም፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 17