ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 13:42-57 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

42. ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደ እቶን እሳት ይጥሏቸዋል።

43. በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሓይ ያበራሉ። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።

44. “መንግሥተ ሰማይ በዕርሻ ውስጥ የተደበቀ ሀብት ትመስላለች፤ አንድ ሰው ባገኛት ጊዜ መልሶ ሸሸጋት፤ ከመደሰቱም የተነሣ ሄዶ፤ ያለውን ሁሉ በመሸጥ ያንን የዕርሻ ቦታ ገዛ።

45. “እንዲሁም መንግሥተ ሰማይ ውብ ዕንቍ የሚፈልግ ነጋዴ ትመስላለች፤

46. እጅግ ውድ የሆነ ዕንቍ ባገኘም ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጦ ገዛው።

47. “ደግሞም መንግሥተ ሰማይ ወደ ባሕር ተጥሎ የዓሣ ዓይነቶችን የያዘ መረብ ትመስላለች፤

48. ዓሣ አጥማጆቹ መረቡ ሲሞላላቸው ጎትተው ወደ ባሕሩ ዳር አወጡት፤ ከዚያም ተቀምጠው ጥሩ ጥሩውን እየለዩ በቅርጫት ውስጥ ጨመሩ፤ መጥፎ መጥፎውን ግን ጣሉት።

49. በዓለም መጨረሻም ልክ እንደዚሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኀጢአተኞችን ከጻድቃን በመለየት፣

50. ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደ እቶን እሳት ይጥሏቸዋል።”

51. ኢየሱስ፣ “ይህ ሁሉ ገብቷችኋል?” አላቸው። እነርሱም፣ “አዎን” አሉት።

52. እርሱም፣ “ስለዚህም የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር የተረዳ ማንኛውም የኦሪት ሕግ መምህር፣ ከከበረ ሀብቱ ክምችት አዲሱንም አሮጌውንም የሚያወጣ ባለንብረት ይመስላል” አላቸው።

53. ኢየሱስ እነዚህን ምሳሌዎች እንደ ጨረሰ፣ ከዚያ ስፍራ ተነሥቶ ሄደ፤

54. ወደ ገዛ አገሩ መጣ፤ በምኵራባቸውም ሕዝቡን ያስተምር ጀመር። እነርሱም በመገረም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው ይህን ጥበብና እነዚህን ታምራት የማድረግ ኀይል ከየት አገኘ?

55. ይህ የአናጢው ልጅ አይደለምን? የእናቱስ ስም ማርያም አይደለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብ፣ ዮሴፍ፣ ስምዖንና ይሁዳ አይደሉምን?

56. እኅቶቹስ ከእኛው ጋር አይደሉምን? ታዲያ ይህ ሰው ይህን ሁሉ ከወዴት አገኘው?”

57. ስለዚህም ሳይቀበሉት ቀሩ።ኢየሱስ ግን፣ “ነቢይ የማይከበረው በራሱ አገርና በራሱ ቤት ብቻ ነው” አላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 13