ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 11:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኢየሱስ ለዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ትእዛዙን ሰጥቶ ከጨረሰ በኋላ ለማስተማርና ለመስበክ ወደ ገሊላ ከተሞች ሄደ።

2. ዮሐንስ በእስር ቤት ሆኖ ክርስቶስ በማድረግ ላይ ያለውን ነገር በሰማ ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ልኮ፣

3. “ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀ።

4. ኢየሱስም፣ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “ሄዳችሁ የምትሰሙትንና የምታዩትን ለዮሐንስ ንገሩት፤

5. ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶች ይራመዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድኾችም የምሥራች እየተሰበከ ነው፤

6. በእኔ የማይሰናከልም ብፁዕ ነው።”

7. የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ከሄዱ በኋላ፣ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “ወደ ምድረ በዳ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ሸምበቆ በነፋስ ሲወዛወዝ?

8. ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ባማረ ልብስ ያጌጠ ሰው? ባማረ ልብስ ያጌጡ በነገሥታት ቤት አሉላችሁ።

9. ታዲያ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይ ልታዩ? አዎን፤ ከነቢይም የሚበልጥ ነው።

10. እንዲህ ተብሎ የተጻፈለት እርሱ ነው፤ “ ‘በፊትህ መንገድህን ያዘጋጅልህ ዘንድ፣ ከአንተ አስቀድሜ መልእክተኛዬን እልካለሁ።’

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 11