ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 10:16-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. “እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ብልኆች እንደ ርግብ የዋሃን ሁኑ።

17. “ሰዎች ይዘው ለፍርድ ወደ ሸንጎ ያቀርቧችኋል፤ በምኵራ ቦቻቸውም ይገርፏችኋል፤ ስለዚህ ከእነርሱ ተጠንቀቁ።

18. በእኔ ምክንያት ወደ ገዦችና ወደ ነገሥታት ትወሰዳላችሁ፤ በእነርሱና በአሕዛብም ፊት ምስክር ትሆናላችሁ።

19. በምትያዙበትም ጊዜ ምን እንናገራለን፣ ምንስ እንመልሳለን ብላችሁ አትጨነቁ፤ በዚያን ጊዜ የምትናገሩት ይሰጣችኋል፤

20. በእናንተ የሚናገረው የሰማዩ አባታችሁ መንፈስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።

21. “ወንድም ወንድሙን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ አባትም ልጁን፤ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ያምፃሉ፤ ያስገድሏቸዋልም።

22. ስለ ስሜ ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል፤ ነገር ግን እስከ መጨረሻ የሚጸና እርሱ ይድናል።

23. በአንድ ስፍራ ሲያሳድዷችሁ ወደ ሌላ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁ፣ የእስራኤልን ከተሞች ሳታዳርሱ የሰው ልጅ ይመጣል።

24. “ደቀ መዝሙር ከመምህሩ፣ ሎሌም ከጌታው አይበልጥም፤

25. ደቀ መዝሙር መምህሩን፣ ሎሌም ጌታውን ከመሰለ ይበቃዋል። ባለቤቱን ‘ብዔልዜቡል’ ካሉት ቤተ ሰዎቹንማ እንዴት አብልጠው አይሏቸውም!

26. “ስለዚህ አትፍሯቸው፤ የተሸፈነ መገለጡ፣ የተደበቀ መውጣቱ አይቀርምና።

27. በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን አውሩት፤ በጆሮአችሁ የሰማችሁትን በአደባባይ አውጁት፤

28. ሥጋን መግደል እንጂ ነፍስን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንና ሥጋን በገሃነም ማጥፋት የሚቻለውን ፍሩ።

29. በአንድ ሳንቲም ከሚሸጡት ሁለት ድንቢጦች አንዲቷ እንኳ ያለ አባታችሁ ፈቃድ ምድር ላይ አትወድቅም።

30. የራስ ጠጕራችሁ እንኳ አንድ ሳይቀር የተቈጠረ ነው።

31. ስለዚህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች ይልቅ ዋጋችሁ የከበረ ነው።

32. “በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ፣ እኔም በሰማይ ባለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤

33. ነገር ግን በሰው ፊት የሚክደኝን፣ እኔም በሰማይ ባለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 10