ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 10:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ጠርቶ ርኵሳን መናፍስትን እንዲያወጡ፣ ደዌንና ሕማምን ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣንን ሰጣቸው።

2. የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ስም የሚከተለው ነው፦ መጀመሪያ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፣ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፣

3. ፊልጶስና በርተሎሜዎስ፣ ቶማስና ቀረጥ ሰብሳቢው ማቴዎስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ታዴዎስ የተባለው ልብድዮስ፣

4. ቀነናዊው ስምዖንና በኋላ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው አስቆሮቱ ይሁዳ።

5. እነዚህን ዐሥራ ሁለቱን ኢየሱስ እንዲህ ከሚል ትእዛዝ ጋር ላካቸው፤ “ወደ አሕዛብ አትሂዱ፤ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ።

6. ይልቁንስ የእስራኤል ቤት ወደሆኑት ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ።

7. ሄዳችሁም፣ ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች’ ብላችሁ ስበኩ።

8. በሽተኞችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አስወጡ፤ በነጻ የተቀበላችሁትንም በነጻ ስጡ።

9. በመቀነታችሁ ወርቅም ሆነ ብር ወይም መዳብ አትያዙ።

10. ለመንገዳችሁም ከረጢት፣ ትርፍ እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አትያዙ፤ ለሠራተኛ የዕለት ጕርሱ ይገባዋልና።

11. “ወደ አንድ ከተማ ወይም መንደር ስትገቡ ሊቀበላችሁ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ፈልጋችሁ በቤቱ ዕረፉ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያው ቈዩ።

12. ወደ ማንኛውም ሰው ቤት ስትገቡ ሰላምታ አቅርቡ።

13. ቤቱም የሚገባው ሆኖ ከተገኘ፣ ሰላማችሁ ይድረሰው፤ የማይገባው ከሆነ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስላችሁ።

14. ማንም ሰው ሊያስተናግዳችሁ ወይም የምትናገሩትን ሊሰማ ፈቃደኛ ካልሆነ፣ ከቤቱ ወይም ከከተማው ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፋችሁ ውጡ።

15. እውነት እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን በዚያች ከተማ ከሚደርሰው ቅጣት ይልቅ በሰዶምና በገሞራ የሚደርሰው ይቀላል።

16. “እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ብልኆች እንደ ርግብ የዋሃን ሁኑ።

17. “ሰዎች ይዘው ለፍርድ ወደ ሸንጎ ያቀርቧችኋል፤ በምኵራ ቦቻቸውም ይገርፏችኋል፤ ስለዚህ ከእነርሱ ተጠንቀቁ።

18. በእኔ ምክንያት ወደ ገዦችና ወደ ነገሥታት ትወሰዳላችሁ፤ በእነርሱና በአሕዛብም ፊት ምስክር ትሆናላችሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 10