ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 8:3-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. እንዲህ እንደ ተራቡ ወደ ቤታቸው ብሰዳቸው አንዳንዶቹ ከሩቅ የመጡ ስለሆኑ በመንገድ ላይ ዝለው ይወድቃሉ።”

4. ደቀ መዛሙርቱም መልሰው፣ “በዚህ ምድረ በዳ እነዚህን ለመመገብ የሚያስችል እንጀራ ከወዴት ይገኛል?” አሉት።

5. እርሱም፣ “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “ሰባት” አሉት።

6. እርሱም፣ መሬት ላይ እንዲቀመጡ ሕዝቡን አዘዘ፤ ሰባቱን እንጀራ ይዞ ካመሰገነ በኋላ ቈርሶ ለሰዎቹ እንዲያድሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሕዝቡ አደሉት።

7. እንዲሁም ትንንሽ ዓሣዎች ነበሯቸው፤ እርሱም ዓሣዎቹን ባርኮ እንዲያድሏቸው አዘዘ።

8. ሕዝቡም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ የተረፈውን ቍርስራሽ ሰባት መሶብ ሙሉ አነሡ።

9. በዚያም አራት ሺህ ያህል ሰዎች ነበሩ፤ ካሰናበታቸውም በኋላ፣

10. ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ዳልማኑታ ወደተባለ ስፍራ ሄደ።

11. ፈሪሳውያንም ወጥተው ከኢየሱስ ጋር ይከራከሩ ጀመር። ሊፈትኑትም ፈልገው ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት።

12. እርሱም በመንፈሱ እጅግ በመቃተት፣ “ይህ ትውልድ ምልክት የሚፈልገው ለምንድን ነው? እውነት እላችኋለሁ፤ ለዚህ ትውልድ ምንም ምልክት አይሰጠውም!” አለ።

13. ከዚያም ትቶአቸው በጀልባ ወደ ማዶ ተሻገረ።

14. ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ስለ ረሱ፣ ከአንድ እንጀራ በቀር በጀልባ ውስጥ ምንም አልነበራቸውም።

15. ኢየሱስም፣ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” ብሎ አዘዛቸው።

16. እነርሱም እርስ በርሳቸው፣ “እንዲህ የሚለን እኮ እንጀራ ስለሌለን ነው” ተባባሉ።

17. ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ፣ እንዲህ አላቸው፤ “እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት ምን ያነጋግራችኋል? አሁንም አታስተውሉምን? ልብስ አትሉምን? ወይስ ልባችሁ ደንድኖአል?

18. ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮ እያላችሁ አትሰሙምን? አታስታውሱምን?

19. አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው በቈረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?”እነርሱም፣ “ዐሥራ ሁለት” አሉት።

20. “ሰባቱንስ እንጀራ ለአራት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” አላቸው።እነርሱም፣ “ሰባት” አሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 8