ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 7:13-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ስለዚህ ለትውልድ በምታስተላልፉት ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ ይህን የመሰለም ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።”

14. ደግሞም ኢየሱስ ሕዝቡን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ስሙኝ፤ ሁላችሁም አስተውሉ፤

15. ከውጭ ወደ ውስጥ ገብቶ ሰውን የሚያረክሰው አንዳች ነገር የለም፤ ይልቁን ሰውን የሚያረክሰው ከራሱ ወደ ውጭ የሚወጣው ነገር ነው፤

16. ሰሚ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ።”

17. ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ምሳሌው ጠየቁት።

18. እርሱም፣ “እናንተም ነገሩ አይገባችሁምን? ከውጭ ወደ ሰው ገብቶ ሊያረክሰው የሚችል አንዳች ነገር የለም፤

19. ወደ ልቡ ሳይሆን ወደ ሆዱ ይገባል፤ ከዚያም ከሰውነቱ ይወጣልና።” ኢየሱስ ይህን በማለቱ ምግብ ሁሉ ንጹሕ መሆኑን ገለጠ።

20. ቀጥሎም፣ እንዲህ አለ፤ “ከሰው የሚወጣ ያ ሰውን ያረክሰዋል፤

21. ከውስጥ፣ ከሰው ልብ የሚወጡት ክፉ ሐሳብ፣ ምንዝር፣ ስርቆት፤ ሰው መግደል፣ ዝሙት፣

22. መስገብገብ፣ ክፋት፣ ማታለል፣ መዳራት፣ ምቀኝነት፣ ስም ማጥፋት፣ ትዕቢት፣ ስንፍና ናቸው።

23. እነዚህ ክፉ ነገሮች ሁሉ ከሰው ይወጣሉ ሰውንም ያረክሱታል።”

24. ከዚያ ተነሥቶ ወደ ጢሮስ አገር ሄደ፤ ወደ አንድ ቤት ገብቶ እዚያ መኖሩን ማንም እንዳያውቅበት ፈለገ፤ ሆኖም እዚያ መኖሩ ሊሸሸግ አልቻለም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 7