ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስ የአይሁድን ውጫዊ ሥርዐት ተቃወመ

1. ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያንና ከኢየሩሳሌም የመጡ አንዳንድ ጸሐፍት በዙሪያው ተሰበሰቡ፤

2. ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ ባልነጻ ማለት ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩ፤

3. ፈሪሳውያንና አይሁድ ሁሉ የአባቶችን ወግ ለመጠበቅ ሲሉ፣ በሥርዐቱ መሠረት እጃቸውን በጥንቃቄ ሳይታጠቡ አይበሉም ነበርና።

4. ከገበያ ሲመለሱም ታጥበው ራሳቸውን ካላነጹ በስተቀር አይበሉም ነበር። እንዲሁም ዋንጫን፣ ማሰሮን፣ ሳሕንና ዐልጋን እንደ ማጠብ ያሉትን ሌሎችን ወጎች ይጠብቁ ነበር።

5. ፈሪሳውያንና ጸሐፍትም፣ “ደቀ መዛሙርትህ እንደ አባቶች ወግ በመኖር ፈንታ ባልታጠበ እጃቸው ለምን እንጀራ ይበላሉ?” ብለው ጠየቁት።

6. እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ኢሳይያስ ስለ እናንተ፣ ስለ ግብዞች በትክክል ተንብዮአል፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤ “ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤

7. በከንቱ ያመልከኛል፤ ትምህርታቸውም ሰው ሠራሽ ሥርዐት ብቻ ነው።’

8. የእግዚአብሔርን ትእዝዛዝ ትታችሁ የሰዎችን ወግና ሥርዐት ታጠብቃላችሁ።”

9. ደግሞም፣ እንዲህ አላቸው፤ “የራሳችሁን ወግ ለመጠበቅ ስትሉ፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የምትተውበት ዘዴ አላችሁ።

10. ሙሴ፣ ‘አባትህንና እናትህን አክብር፤ አባቱን ወይም እናቱን የሚሳደብ ፈጽሞ ይሙት ብሎ ነበርና፤

11. እናንተ ግን አንድ ሰው አባቱን ወይም እናቱን፣ ‘ከእኔ ማግኘት የሚገባችሁን ርዳታ ሁሉ ቍርባን ይኸውም መባ አድርጌአለሁ ቢላቸው፣

12. እናንተም ይህ ሰው ለአባቱም ሆነ ለእናቱ ከዚህ በኋላ ምንም ነገር እንዲያደርግ አትፈቅዱለትም።

13. ስለዚህ ለትውልድ በምታስተላልፉት ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ ይህን የመሰለም ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።”

14. ደግሞም ኢየሱስ ሕዝቡን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ስሙኝ፤ ሁላችሁም አስተውሉ፤

15. ከውጭ ወደ ውስጥ ገብቶ ሰውን የሚያረክሰው አንዳች ነገር የለም፤ ይልቁን ሰውን የሚያረክሰው ከራሱ ወደ ውጭ የሚወጣው ነገር ነው፤

16. ሰሚ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ።”

17. ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ምሳሌው ጠየቁት።

18. እርሱም፣ “እናንተም ነገሩ አይገባችሁምን? ከውጭ ወደ ሰው ገብቶ ሊያረክሰው የሚችል አንዳች ነገር የለም፤

19. ወደ ልቡ ሳይሆን ወደ ሆዱ ይገባል፤ ከዚያም ከሰውነቱ ይወጣልና።” ኢየሱስ ይህን በማለቱ ምግብ ሁሉ ንጹሕ መሆኑን ገለጠ።

20. ቀጥሎም፣ እንዲህ አለ፤ “ከሰው የሚወጣ ያ ሰውን ያረክሰዋል፤

21. ከውስጥ፣ ከሰው ልብ የሚወጡት ክፉ ሐሳብ፣ ምንዝር፣ ስርቆት፤ ሰው መግደል፣ ዝሙት፣

22. መስገብገብ፣ ክፋት፣ ማታለል፣ መዳራት፣ ምቀኝነት፣ ስም ማጥፋት፣ ትዕቢት፣ ስንፍና ናቸው።

23. እነዚህ ክፉ ነገሮች ሁሉ ከሰው ይወጣሉ ሰውንም ያረክሱታል።”

ሲሮፊኒቃዊቷ ሴት

24. ከዚያ ተነሥቶ ወደ ጢሮስ አገር ሄደ፤ ወደ አንድ ቤት ገብቶ እዚያ መኖሩን ማንም እንዳያውቅበት ፈለገ፤ ሆኖም እዚያ መኖሩ ሊሸሸግ አልቻለም።

25. ወዲያው ግን ትንሺቱ ልጇ በርኩስኸ መንፈስ የተያዘችባት አንዲት ሴት ስለ እርሱ ሰምታ መጣችና በእግሩ ላይ ወደቀች።

26. ሴትየዋም ግሪካዊት፣ በትውልዷም ሲሮፊኒቃዊት ነበረች። እርሷም ኢየሱስ ጋኔኑን ከልጇ እንዲያስወጣላት ለመነችው።

27. እርሱ ግን፣ “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መጣል ተገቢ ስላልሆነ፣ መጀመሪያ ልጆቹ ጠግበው ይብሉ” አላት።

28. እርሷም መልሳ፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ ውሾችም ከገበታ በታች ሆነው የልጆችን ትራፊ ይበላሉ” አለችው።

29. እርሱም፣ “ስለዚህ ይህን ስላልሽ ሂጂ፤ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቶአል” አላት።

30. እርሷም ወደ ቤቷ ስትመለስ ልጇ ዐልጋ ላይ ተኝታ፣ ጋኔኑም ለቆአት አገኘቻት።

የደንቈሮውና የድዳው መፈወስ

31. ከዚያም ኢየሱስ ከጢሮስ አገር ተነሥቶ፣ በሲዶና በኩል አድርጎ ዐሥር ከተማ በተባለው አገር በማለፍ ወደ ገሊላ ባሕር መጣ።

32. በዚያም ሰዎች ደንቈሮና ዲዳ የሆነ አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ እጁንም እንዲጭንበት ለመኑት።

33. ኢየሱስም ሰውየውን ከሕዝቡ ለይቶ ከወሰደው በኋላ፣ ጣቶቹን በጆሮው አስገባ፤ ከዚያም እንትፍ ብሎ የሰውየውን ምላስ ዳሰሰ።

34. ወደ ሰማይም ተመልክቶ ቃተተና፣ “ኤፍታህ!” አለው፤ ይኸውም፣ “ተከፈት” ማለት ነው።

35. ወዲያውም ጆሮዎቹ ተከፈቱ፤ ምላሱም ተፈቶ አጥርቶ መናገር ጀመረ።

36. ኢየሱስ ይህን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው፤ ሆኖም እርሱ እንዳይናገሩ ባዘዛቸው መጠን፣ ነገሩን አስፍተው አወሩት።

37. ሕዝቡም ከመጠን በላይ በመደነቅ፣ “ያደረገው ሁሉ ጥሩ ነው፤ ደንቈሮዎች እንዲሰሙ፣ ድዳዎች እንዲናገሩ እንኳ አድርጎአል” አሉ።