ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 5:6-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ይህም ሰው ኢየሱስን ከሩቅ ባየው ጊዜ ወደ እርሱ ሮጦ ከፊቱ ተንበርክኮ ሰገደለት፤

7. በታላቅ ድምፅ ጮኾም፣ “አንተ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኔ ምን አለህ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር ይዤሃለሁ” አለው።

8. ይህንንም ያለው ኢየሱስ፣ “አንተ ርኩስ መንፈስ ከዚህ ሰው ውጣ!” ብሎት ስለ ነበር ነው።

9. ከዚያም ኢየሱስ፣ “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው። “ብዙ ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው” አለው።

10. ከአገር እንዳያስወጣቸውም አጥብቆ ለመነው።

11. በአቅራቢያውም በሚገኝ ኰረብታ ላይ ትልቅ የዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር።

12. ርኵሳን መናፍስቱም ኢየሱስን፣ “ወደ ዐሣማዎቹ ስደደን፤ እንድንገባባቸውም ፍቀድልን” ብለው ለመኑት።

13. እርሱም ፈቀደላቸው። ርኵሳን መናፍስቱም ወጥተው በዐሣማዎቹ ገቡባቸው፤ ሁለት ሺህ ያህል ዐሣማዎችም በገደሉ አፋፍ በመንደርደር ቊልቊል ወርደው በባሕር ውስጥ ሰጠሙ።

14. እረኞቹ ሸሽተው ሄዱ፤ ወሬውን በከተማና በገጠር አዳረሱት፤ ሕዝቡም የሆነውን ለማየት ካለበት ወጣ።

15. ወደ ኢየሱስም በመጡ ጊዜ፣ የአጋንንት ሰራዊት አድረውበት የነበረው ሰው፣ ልብስ ለብሶና አእምሮው ተመልሶለት በዚያ ተቀምጦ አዩት፤ ፈሩም።

16. ይህን ያዩ ሰዎችም አጋንንት ስላ ደረበት ሰው የተደረገውንና ስለ ዐሣማዎቹም ለሕዝቡ አወሩ።

17. ከዚያም ሕዝቡ አገራቸውን ለቆ እንዲሄድላቸው ኢየሱስን ይለምኑት ጀመር።

18. ኢየሱስ ወደ ጀልባዪቱ በሚገባበት ጊዜ፣ አጋንንት አድሮበት የነበረው ሰው አብሮት ለመሄድ ለመነው።

19. ኢየሱስ አልፈቀደለትም፤ ነገር ግን፣ “ወደ ቤትህ ሂድ፣ ለዘመዶችህም ጌታ ምን ያህል ታላቅ ነገር እንዳደረገልህና ያሳየህን ምሕረት ንገራቸው” አለው።

20. ሰውየውም ሄደ፤ ኢየሱስ ያደረገለትን ነገር ሁሉ ዐሥር ከተማ በተባለው አገር ያወራ ጀመር፤ የሰሙትም ሁሉ ተደነቁ።

21. ኢየሱስ እንደ ገና በጀልባ ወደ ማዶ በተሻገረ ጊዜ፣ ብዙ ሕዝብ በዙሪያው ተሰባሰበ፤ በባሕሩ ዳርቻም እንዳለ፣

22. ከምኵራብ አለቆች አንዱ ኢያኢሮስ የተባለው ወደዚያ መጥቶ ስለ ነበር፣ ኢየሱስን ባየው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቆ፣

23. “ትንሿ ልጄ በሞት አፋፍ ላይ ናትና ድና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” በማለት አጥብቆ ለመነው።

24. ኢየሱስም አብሮት ሄደ።ብዙ ሕዝብም ዙሪያውን እያጨናነቀው ተከተለው።

25. ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የኖረችም ሴት በዚያ ነበረች፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 5