ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 5 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አጋንንት ያደሩበት ሰው መፈወሱ

1. ባሕሩን ተሻግረው ጌርሴኖን ወደተባለ አገር መጡ።

2. ኢየሱስ ከጀልባ እንደ ወረደ፣ ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ከመቃብር ቦታ ወጥቶ ሊገናኘው ወደ እርሱ መጣ።

3. ይህ ሰው በመቃብር ቦታ ውስጥ የሚኖርና ማንም በሰንሰለት እንኳ ሊያስረው የማይችል ነበር።

4. ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበር፤ ነገር ግን የእጅ ሰንሰለቱን ይበጥስ፣ የእግር ብረቱንም ይሰብር ነበር። ማንም ይዞ ሊያቈየው የሚችል አልነበረም።

5. በመቃብሮቹና በተራራዎቹ መካከል ቀንና ሌሊት እየተዘዋወረ በመጮኽ ሰውነቱን በድንጋይ ይቈራርጥ ነበር።

6. ይህም ሰው ኢየሱስን ከሩቅ ባየው ጊዜ ወደ እርሱ ሮጦ ከፊቱ ተንበርክኮ ሰገደለት፤

7. በታላቅ ድምፅ ጮኾም፣ “አንተ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኔ ምን አለህ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር ይዤሃለሁ” አለው።

8. ይህንንም ያለው ኢየሱስ፣ “አንተ ርኩስ መንፈስ ከዚህ ሰው ውጣ!” ብሎት ስለ ነበር ነው።

9. ከዚያም ኢየሱስ፣ “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው። “ብዙ ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው” አለው።

10. ከአገር እንዳያስወጣቸውም አጥብቆ ለመነው።

11. በአቅራቢያውም በሚገኝ ኰረብታ ላይ ትልቅ የዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር።

12. ርኵሳን መናፍስቱም ኢየሱስን፣ “ወደ ዐሣማዎቹ ስደደን፤ እንድንገባባቸውም ፍቀድልን” ብለው ለመኑት።

13. እርሱም ፈቀደላቸው። ርኵሳን መናፍስቱም ወጥተው በዐሣማዎቹ ገቡባቸው፤ ሁለት ሺህ ያህል ዐሣማዎችም በገደሉ አፋፍ በመንደርደር ቊልቊል ወርደው በባሕር ውስጥ ሰጠሙ።

14. እረኞቹ ሸሽተው ሄዱ፤ ወሬውን በከተማና በገጠር አዳረሱት፤ ሕዝቡም የሆነውን ለማየት ካለበት ወጣ።

15. ወደ ኢየሱስም በመጡ ጊዜ፣ የአጋንንት ሰራዊት አድረውበት የነበረው ሰው፣ ልብስ ለብሶና አእምሮው ተመልሶለት በዚያ ተቀምጦ አዩት፤ ፈሩም።

16. ይህን ያዩ ሰዎችም አጋንንት ስላ ደረበት ሰው የተደረገውንና ስለ ዐሣማዎቹም ለሕዝቡ አወሩ።

17. ከዚያም ሕዝቡ አገራቸውን ለቆ እንዲሄድላቸው ኢየሱስን ይለምኑት ጀመር።

18. ኢየሱስ ወደ ጀልባዪቱ በሚገባበት ጊዜ፣ አጋንንት አድሮበት የነበረው ሰው አብሮት ለመሄድ ለመነው።

19. ኢየሱስ አልፈቀደለትም፤ ነገር ግን፣ “ወደ ቤትህ ሂድ፣ ለዘመዶችህም ጌታ ምን ያህል ታላቅ ነገር እንዳደረገልህና ያሳየህን ምሕረት ንገራቸው” አለው።

20. ሰውየውም ሄደ፤ ኢየሱስ ያደረገለትን ነገር ሁሉ ዐሥር ከተማ በተባለው አገር ያወራ ጀመር፤ የሰሙትም ሁሉ ተደነቁ።

የሞተችው ልጅና የታመመችው ሴት

21. ኢየሱስ እንደ ገና በጀልባ ወደ ማዶ በተሻገረ ጊዜ፣ ብዙ ሕዝብ በዙሪያው ተሰባሰበ፤ በባሕሩ ዳርቻም እንዳለ፣

22. ከምኵራብ አለቆች አንዱ ኢያኢሮስ የተባለው ወደዚያ መጥቶ ስለ ነበር፣ ኢየሱስን ባየው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቆ፣

23. “ትንሿ ልጄ በሞት አፋፍ ላይ ናትና ድና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” በማለት አጥብቆ ለመነው።

24. ኢየሱስም አብሮት ሄደ።ብዙ ሕዝብም ዙሪያውን እያጨናነቀው ተከተለው።

25. ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የኖረችም ሴት በዚያ ነበረች፤

26. በብዙ ባለ መድኀኒቶች ዘንድ በመንከራተት ያላትን ሁሉ ብትጨርስም፣ ሕመሙ ባሰባት እንጂ አልተሻላትም ነበር።

27. ስለ ኢየሱስም በሰማች ጊዜ፣ ከበስተ ኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ነካች፤

28. ምክንያቱም፣ “እንደምንም ብዬ ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እፈወሳለሁ” የሚል እምነት ነበራት።

29. የሚፈሰው ደሟ ወዲያውኑ ቆመ፤ ከሥቃይዋ መገላገሏም በሰውነቷ ታወቃት።

30. ወዲያውኑ ኢየሱስ፣ ኀይል ከእርሱ እንደ ወጣ ዐውቆ፤ ወደ ሕዝቡ ዘወር በማለት፣ “ልብሴን የነካው ማን ነው?” አለ።

31. ደቀ መዛሙርቱም፣ “ሕዝቡ ተጨናንቆ ሲጋፋህ እያየህ፣ ‘ማን ነው የነካኝ?’ እንዴት ትላለህ?” አሉት።

32. ኢየሱስ ግን ይህንን ያደረገው ማን እንደሆነ ለማየት ዙሪያውን ተመለከተ።

33. ሴትየዋም ምን እንደ ተደረገላት ባወቀች ጊዜ እየፈራችና እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ እውነቱንም ሁሉ ነገረችው።

34. እርሱም፣ “ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤ ከሥቃይሽም ዕረፊ” አላት።

35. ኢየሱስም በመነጋገር ላይ እያለ፣ ሰዎች ከምኵራቡ አለቃ ከኢያኢሮስ ቤት መጥተው፣ “ልጅህ ሞታለች፤ ከእንግዲህ መምህሩን ለምን ታደክመዋለህ?” አሉት።

36. ኢየሱስ ግን ሰዎቹ የተናገሩትን ችላ በማለት የምኵራቡን አለቃ፣ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ፤” አለው።

37. ከጴጥሮስና ከያዕቆብ እንዲሁም ከያዕቆብ ወንድም ከዮሐንስ በቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም።

38. ወደ ምኵራቡ አለቃ ቤት እንደ ደረሱ፣ ኢየሱስ ግርግሩንና ሰዎቹም ዋይ ዋይ እያሉ አምርረው ሲያለቅሱ ተመለከተ።

39. ወደ ቤትም ገብቶ፣ “ይህ ሁሉ ግርግርና ልቅሶ ምንድን ነው? ብላቴናዪቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው።

40. ሰዎቹ ግን ሣቁበት።ሰዎቹን ሁሉ ከቤት ካስወጣ በኋላ፣ የብላቴናዪቱን አባትና እናት እንዲሁም አብረውት የመጡትን ደቀ መዛሙርት አስከትሎ ብላቴናዪቱ ወዳለችበት ገባ።

41. ከዚያም የብላቴናዪቱን እጅ ይዞ፣ “ጣሊታ ቁሚ!” አላት፤ ትርጒሙም፣ “አንቺ ልጅ ተነሺ” ማለት ነው።

42. ብላቴናዪቱም ወዲያውኑ ተነሥታ ቆመች፤ ወዲያ ወዲህም ሄደች። ዕድሜዋም ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር። ሰዎቹም በሁኔታው እጅግ ተደነቁ።

43. እርሱም ይህን ነገር ማንም እንዳያውቅ አጥብቆ አስጠነቀቃቸው፤ የሚበላ ነገር እንዲሰጧትም ነገራቸው።