ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 2:9-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ሽባውን፣ ‘ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል’ ከማለትና፣ ‘ተነሥተህ ዐልጋህን ተሸክመህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀላል?

10. ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ለማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ” በማለት ሽባውን፣

11. “ተነሥተህ ዐልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው።

12. እርሱም ተነሥቶ ሁሉም እያዩት ዐልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ በስፍራው የነበሩትም ሁሉ በሁኔታው በመደነቅ፣ “የዚህ ዐይነት ነገር ፈጽሞ አይተን አናውቅም!” በማለት ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀረቡ።

13. ኢየሱስም ዳግም ወደ ባሕሩ ዳርቻ ወጣ፤ ሕዝቡም በብዛት ወደ እርሱ መጡ፤ እርሱም አስተማራቸው።

14. በዚያም ሲያልፍ የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን በቀረጥ መቀበያው ስፍራ ተቀምጦ አየውና፣ “ተከተለኝ” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ተከተለው።

15. በማቴዎስ ቤት በማእድ ተቀምጦ ሳለ፣ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኀጢአተኞች ተከትለውት ስለ ነበር፣ ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይመገቡ ነበር።

16. ከፈሪሳውያን ወገን የነበሩ ጸሐፍት ከኀጢአተኞችና ከቀረጥ ሰብሳቢዎች ጋር ሲበላ ባዩት ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱን “ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኀጢአተኞች ጋር ለምን ይበላል?” ሲሉ ጠየቋቸው።

17. ኢየሱስም የሚናገሩትን ሰምቶ፣ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም፤ እኔ ኀጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ወደ ንስሓ ልጠራ አልመጣሁም” አላቸው።

18. የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጾሙ ነበር፤ አንዳንድ ሰዎችም መጥተው ኢየሱስን፣ “የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ሲጾሙ፣ የአንተ ደቀ መዛሙርት የማይጾሙት ለምንድን ነው?” አሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 2